Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 8:09

[1] ለሕዝቡም ቃሉን ነግሮ ከፈጸመ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።

[2] አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ አገልጋዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር፤ እርሱም በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነበር።

[3] የጌታችን የኢየሱስንም ነገር በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ አገልጋዩን እንዲያድንለት ይማልዱት ዘንድ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከ።

[4] ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስም መጥተው ማለዱት፤ እንዲህም አሉት ፥ “ፈጥነህ ውረድ፤ ይህን ልታደርግለት ይገባዋልና።

[5] እርሱ ወገናችንን ይወዳልና፤ ምኵuራባችንንም ሠርቶልናልና።”

[6] ጌታችን ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ፥ የመቶ አለቃዉ ወዳጆቹን እንዲህ ብሎ ላከ ፥ “አቤቱ፥ አትድከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና።

[7] እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይገባኝም፤ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ፤ ብላቴናዬም ይድናል።

[8] እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም እንዲህ አድርግ ብለው ያደርጋል።”

[9] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ከእርሱ በሰማ ጊዜ አደነቀው፤ ዘወር ብሎም ይከተሉት ለነበሩት ሕዝብ ፥ “እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው ሰው አላገኘሁም ” አላቸው።

[10] የተላኩትም በተመለሱ ጊዜ ብላቴናውን ድኖ አገኙት።

[11] በማግሥቱም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም አብረውት ሄዱ።

[12] ወደ ከተማው በር በደረሰ ጊዜም እነሆ፥ ያንዲት መበለት ሴት ልጅ ሙቶ ሬሳውን ተሸክመው ሲሄዱ አገኘ፤ ይኸውም ለእናቱ አንድ ነበረ፤ ብዙዎችም የከተማ ሰዎች አብረዋት ነበሩ።

[13] ጌታችንም በአያት ጊዜ አዘነላትና ፥ “አታልቅሺ ” አላት።

[14] ቀርቦም ቃሬዛውን ያዘ፤ የተሸከሙትም ቆሙ፤ እርሱም ፥ “አንተ ጐበዝ ተነሥ እልሃለሁ ” አለው።

[15] የሞተውም ተነሥቶ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ፤ ለእናቱም ሰጣት።

[16] ሁሉም ፈሩ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ ፥ “ታላቅ ነቢይ ተነሣልን፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐብኝቶአልና።”

[17] ይህም የእርሱ ዜና በይሁዳ ሀገሮች ሁሉና በአውራጃዋ ሁሉ ተሰማ።

[18] ይህንም ሁሉ ደቀ መዝሙርቱ ለዮሐንስ ነገሩት።

[19] ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ ፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” ብሎ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ላካቸው።

[20] መልእክተኟችም ወደ እርሱ ደርሰው ፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ? ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል ” አሉት።

[21] ያንጊዜም ብዙዎችን ከደዌአቸውና ከሕመማቸው ከክፉዎች አጋንንትም ፈወሳቸው፤ ለብዙዎች ዕውራንም እንዲያዩ ብርሃንን ሰጣቸው።

[22] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል።

[23] በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።”

[24] የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ከሄዱ በኋላ ለሕዝቡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ጀመር ፥ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዝ ሸንበቆን ነውን?

[25] ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? እነሆ፥ በክብር ልብስ ያጌጡስ በነገሥታት ቤት አሉ።

[26] ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ነቢይን ነውን? አዎን፥ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም ይበልጣል።

[27] እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፥ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነው።

[28] እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም አልተነሣም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል።”

[29] ሕዝቡም ሁሉ ቀራጮችም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ጻድቅ ነው አሉት፤ የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበርና።

[30] ፈሪሳውያንና የሕግ ጻፎች ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቃወሙ፤ በእርሱ አልተጠመቁምና።

[31] “እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ?

[32] በገበያ ተቀምጠው ባልንጀሮቻቸውን ጠርተው ፥ “አቀነቀንላችሁ፥ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾም አወጣንላችሁ፥ አላለቀሳችሁምም የሚሉአቸው ልጆችን ይመስላሉ።

[33] መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላ ወይንም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና ጋኔን አለበት አላችሁት።

[34] የሰው ልጅም እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን እነሆ፥ በላተኛና ወይን ጠጪ ሰው፥ የኃጥኣንና የቀራጮች ወዳጅ አላችሁት።

[35] ጥበብም ከልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።”

[36] ከፈሪሳውያንም አንዱ በእርሱ ዘንድ ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ወደ ፈሪሳዊውም ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ።

[37] እነሆ፥ ከዚያች ከተማ ሰዎችም አንዲት ኀጢአተኛ ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ዐውቃ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ገዝታ መጣች።

[38] በስተኋላውም በእግሮቹ አጠገብ ቆማ አለቀሰች፤ እግሮቹንም በእንባዋ ታርስ ነበር፥ በራስ ጠጕuርዋም እግሮቹን ታብሰውና ትስመው፥ ሽቱም ትቀባው ነበር።

[39] የጠራው ፈሪሳዊም ባየ ጊዜ በልቡ ዐሰበ፤ እንዲህም አለ ፥ “ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባላወቀም ነበርን? ኀጢአተኛ ናትና።”

[40] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ ” አለው፤ እርሱም ፥ “መምህር ሆይ፥ ተናገር ” አለው።

[41] እርሱም እንዲህ አለው ፥ “ለአንድ አበዳሪ ሁለት ባለ ዕዳዎች ነበሩት፤ በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ በሁለተኛውም አምሳ።

[42] የሚከፍሉትም ባጡ ጊዜ ለሁለቱም ተወላቸው፤ እንግዲህ ከሁለቱ አብልጦ ሊወደው የሚገባው ማንኛው ነው?”

[43] ስምዖንም መልሶ ፥ “ብዙውን የተወለት ነው እላለሁ ” አለው፤ እርሱም ፥ “መልካም ፈረድህ ” አለው።

[44] ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው ፥ “ይህቺን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ለእግሮቼ ውኃ ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን አልቅሳ በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጕuርዋም አበሰች።

[45] አንተስ ሰላምታ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቌረጠችም።

[46] አንተ ራሴን እንኳ ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባችኝ።

[47] ስለዚህም እልሃለሁ፤ ብዙ ኀጢኣቷ ተሰርዮላታል፤ በብዙ ወድዳለችና፤ ጥቂት የሚወድድ ጥቂት ይሰረይለታል፤ ብዙ የሚወድድም ብዙ ይሰረይለታል።”

[48] ሴቲቱንም ፥ “ኀጢኣትሽ ተሰረየልሽ ” አላት።

[49] በማዕዱ የተቀመጡትም እርስ በርሳቸው ፥ “ኀጢአትን የሚያስተሰርይ ይህ ማነው?” ይሉ ጀመር።

[50] ሴቲቱንም አላት ፥ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ።”

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters