[1] በዚያን ጊዜም እጅግ ብዙ ሰዎች እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ ይላቸው ጀመረ ፥ “አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፤ ይኸውም ግብዝነት ነው።
[2] የማይገለጥ የተሰወረ፥ የማይታይም የተሸሸገ የለምና።
[3] በጨለማ የምትናገሩት በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትንሾካሾኩት በሰገነት ይሰበካል።
[4] ለእናንተ ለወዳጆቼ እላችኋለሁ ፥ ሥጋችሁን የሚገድሉትን አትፍሩአቸው፤ ከዚህም የበለጠ ማድረግ የሚችሉት የላቸውም።
[5] ነገር ግን፤ የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ እናንተስ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ሊጥል ሥልጣን ያለውን ፍሩት፤ አዎ፥ እላችኋለሁ፤ እርሱን ፍሩ።
[6] አምስት ወፎች በሁለት ሻሚ መሐለቅ ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲቱ ስንኳን በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም።
[7] የእናንተስ የራስ ጠጕuራችሁ ሁሉ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ወፎች እናንተ ትበልጣላችሁና።
[8] “እላችኋለሁ ፥ በሰው ፊት የሚያምንብኝን ሁሉ እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት አምነዋለሁ።
[9] በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ።
[10] በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም አይሰረይለትም።
[11] ወደ አደባባይ ወደ ሹሞቹና ወደ ነገሥታቱ፥ ወደ መኳንንቱም በሚወስዱአችሁ ጊዜ የምትሉትንና የምትናገሩትን አታስቡ።
[12] ያንጊዜ በእናንተ ላይ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነውና።”
[13] ከሕዝቡም አንዱ ፥ “መምህር ሆይ፥ ርስቴን እንዲያካፍለኝ ለወንድሜ ንገረው ” አለው።
[14] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተ ሰው፥ በእናንተ ላይ አካፋይና ዳኛ አድርጎ ማን ሾመኝ?” አለው።
[15] “ዕወቁ፤ ከቅሚያም ሁሉ ተጠበቁ፤ ሰው የሚድን ገንዘብ በማብዛት አይደለምና ” አላቸው።
[16] ምሳሌም መሰለላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እርሻው የበጀለትና ሀገር የተመቸው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ።
[17] እህሌን የማኖርበት የለኝምና ምን ላድርግ ብሎ በልቡ ዐሰበ።
[18] እርሱም አለ ፥ እንዲህ አደርጋለሁ፤ የቀድሞውን ጎተራዬን አፈርሳለሁ፤ ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ጎተራም እሠራለሁ፤ እህሌንና በረከቴንም በዚያ እሰበስባለሁ።
[19] ሰውነቴንም እንዲህ እላታለሁ ፥ ሰውነቴ ሆይ፥ የሰበሰብሁልሽ ለብዙ ዓመታት የሚበቃሽ የደለበ ብዙ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ወዲህ ዕረፊ፥ ብዪ፤ ጠጪም፤ ደስም ይበልሽ።
[20] እግዚአብሔርም ፥ አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህን ከሥጋህ ለይተው ይወስዷታል፤ እንግዲህ ያጠራቀምኸው ለማን ይሆናል? አለው።
[21] ሀብትን ለራሱ የሚሰበስብ፤ ሀብቱም ከእግዚአብሔር ያልሆነ እንዲሁ ነው።”
[22] ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው ፥ “ስለዚህ እላችህWaለሁ፤ ለነፍሳችሁ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት፥ ለሰውነታችሁም ስለምትለብሱት አትጨነቁ።
[23] ነፍስ ከምግብ ትበልጣለችና፤ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና።
[24] የማይዘሩትንና የማያጭዱትን፥ ጎተራና ጕuድጓድ የሌላቸውን የቐራዎችን ጫጭቶች ተመልከቱ፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል፤ እንግዲህ እናንተ ከወፎች እንዴት እጅግ አትበልጡም?
[25] ከእናንተስ ዐስቦ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚቻለው ማነው?
[26] ይህን ቀላሉን የማትችሉ ከሆነ በሌላው ለምን ትጨነቃላችሁ?
[27] እነሆ፥ አበባዎችን እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይፈትሉም፤ አይደክሙም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ዘመን ሁሉ ከእነርሱ እንደ አንዱ አልለበሰም።
[28] እነሆ፥ ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የአበባ አገዳ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያደርገው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ ለእናንተማ እንዴት አብልጦ አያደርግላችሁ?
[29] እናንተም የምትበሉትንና የምትጠጡትን አትፈልጉ፤ ወዲያና ወዲህም አትበሉ፤ አትጨነቁለትም።
[30] ይህን ሁሉ በውጭ ያሉ የዓለም አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተስ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንደምትሹት ያውቃል።
[31] ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ ሹ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
[32] “አንተ ታናሽ መንጋ፥ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥቱን ሊሰጣችሁ ወዶአልና።
[33] ሀብታችሁን ሸጣችሁ ምጿት ስጡ፤ ሌባ በማያገኝበት ነቀዝም በማያበላሽበት፥ የማያረጅ ከረጢት፥ የማያልቅም መዝገብ በሰማያት ለእናንተ አድርጉ።
[34] መዝገባችሁ ካለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና።
[35] “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን።
[36] እናንተም፥ በመጣና በር በመታ ጊዜ ወዲያው ይከፍቱለት ዘንድ ከሰርግ እስኪመለስ ጌታቸውን እንደሚጠብቁ ሰዎች ሁኑ።
[37] ጌታቸው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርጉና ሲተጉ የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ወገቡን ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ እየተመላለሰም ያገለግላቸዋል።
[38] ከሌሊቱ በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል ቢመጣና እንዲሁ ቢያገኛቸው እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው።
[39] ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ሌባ የሚመጣበትን ጊዜ ቢያውቅ ተግቶ በጠበቀ፥ ቤቱንም እንዲቈፍሩት ባልፈቀደም ነበር።
[40] እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ ባልጠረጠራችሁበት ሰዓት ይመጣልና።”
[41] ጴጥሮስም ፥ “አቤቱ፥ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ነውን? ወይስ ለሁሉ ነው?” አለው።
[42] ጌታችንም እንዲህ አለው ፥ “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን?
[43] ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው።
[44] እውነት እላችኋለሁ፥ በሀብቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል፤
[45] ነገር ግን ያ ክፉ አገልጋይ በልቡ ፥ ጌታዬ ቶሎ አይመጣም ቢል፥ በጌታው ቤት ያሉትንም ወንዶችንና ሴቶችን አገልጋዮች ሊደበድብና ሊያጕuላላ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ ቢሰክርም፥
[46] የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠረጠረው ዕለት፥ ባላወቀውም ሰዓት መጥቶ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ ዕድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርገዋል።
[47] የጌታውን ፈቃድ ዐውቆ እንደ ፈቃዱ የማይሠራና የማያዘጋጅ የዚያ አገልጋይ ቅጣቱ ብዙ ነው።
[48] ያላወቀ ግን ባይሠራም ቅጣቱ ጥቂት ነው፤ ብዙ ከሰጡት ብዙ ይፈልጉበታልና። ጥቂት ከሰጡትም ጥቂት ይፈልጉበታልና።
[49] “በምድር ላይ እሳትን አምጥቼአለሁ፤ እርስዋን ከማንደድ በቀር ምን እሻለሁ?
[50] ነገር ግን፤ የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፤ እስክፈጽማትም ድረስ እጅግ እታገሣለሁ።”
[51] ሕዝቡንም እንዲህ አላቸው ፥ “ለምድር ሰላምን ያመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፤ አይደለም፤ ሰይፍንና መለያየትን ነው እንጂ።
[52] ከእንግዲህስ ወዲህ አምስት ሰዎች በአንድ ቤት ቢኖሩ ሦስቱ ከሁለቱ፥ ሁለቱም ከሦስቱ ይለያሉ፤
[53] አባት ከልጁ፥ ልጅም ከአባቱ ይለያል፤ እናት ከልጅዋ፥ ልጅም ከእናቷ ትለያለች፤ አማት ከምራቷ፥ ምራትም ከአማቷ ትለያለች።”
[54] ከዚህም በኋላ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው ፥ “ደመና በምዕራብ በኩል ደምኖ ባያችሁ ጊዜ ‘ዝናም ይመጣል ’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል።
[55] የአዜብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም ‘ድርቅ ይሆናል፤’ ትላላችሁ እንዲሁም ይሆናል።
[56] እናንት ግብዞች! የሰማዩንና የምድሩን ፊት መመርመር ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እነዚህን ዘመናት መመርመርን እንዴት አታውቁም?
[57] እናንተ ራሳችሁ እውነቱን ለምን አትፈርዱም?
[58] ከባለጋራህ ጋር ወደ ሹም በምትሄድበት ጊዜ ወደ ዳኛ እንዳይወስድህ በመንገድ ሳለህ ታረቅ፤ ዕዳህንም ክፈል፤ ዳኛው ለሎሌው አሳልፎ ይሰጥሃልና። ሎሌውም በወኅኒ ቤት ያስርሃል።
[59] ያለብህን የመጨረሻዋን ግማሽ ሣንቲም ቢሆን እስክትጨርስ ድረስ አትወጣም እልሃለሁ።”