[1] በሙዳየ ምጿቱ መባቸውን የሚያገቡ ባለጠጎችን አየ።
[2] አንዲት ድሃ መበለትም ሁለት መሐለቅ ስታስገባ አየ።
[3] እንዲህም አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህቺ ድሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብዝታ ለእግዚአብሔር መባ አገባች።
[4] እነዚህ ሁሉ ከተረፋቸው ለእግዚአብሔር መባ አግብተዋልና፤ ይህቺ ግን ከድህነቷ ያላትን ጥሪቷን ሁሉ አገባች።”
[5] ስለ ቤተ መቅደስም ድንጋዩ ያማረ ነው፥ አሠራሩም ያጌጠ ነው የሚሉት ነበሩ።
[6] እንዲህም አላቸው ፥ “ይህን ታያላችሁን? በእዚህ ቦታ ድንጋይ በድንጋይ ላይ የማይተውበትና ሳይፈርስ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል።”
[7] እነርሱም ፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ መቼ ይደረጋል? ይህስ የሚሆንበት ጊዜው፥ ምልክቱስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
[8] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ፤ ጊዜውም ደርሶአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና እንዳያስቱአችሁ ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም ተከትላችሁ አትሂዱ።
[9] ጦርነትንና ጠብን፥ ክርክርንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን ወዲያው የሚፈጸም አይደለም።”
[10] እንዲህም አላቸው ፥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ ይነሣሉ።
[11] በየሀገሩ ታላቅ የምድር መነዋወጥና ራብ፥ በሰውም ላይ በሽታና ፍርሀት ይመጣል፤ በሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።
[12] ከዚህም ሁሉ አስቀድሞ ይይዙአችኋል፤ ወደ አደባባዮችም ይወስዱአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ያስሩአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ መሳፍንት ይወስዱአችኋል።
[13] ይህም በእነርሱ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል።
[14] ዕወቁ፤ የምትናገሩትንም በልባችሁ አታስቡ።
[15] በእናንተ ላይ የሚነሡ ሊመልሱላችሁና ሊከራከሯችሁ እንዳይችሉ እኔ አፍንና ጥበብን እሰጣችኋለሁ።
[16] ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ወዳጆቻችሁና ባልንጀሮቻችሁ አሳልፈው ይሰጡአችኋል።
[17] ሁሉም ስለ ስሜ ይጠሉአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም።
[18] ነገር ግን ከራስ ጠጕuራችሁ አንዲቱ እንኳ አትጠፋም።
[19] በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ።
[20] “ኢየሩሳሌምን ጭፍሮች ከብበዋት ባያችሁ ጊዜ ጥፋቷ እንደ ደረሰ ዕወቁ።
[21] ያንጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ፤ በመካከልዋ ያሉም ከእርስዋ ይውጡ፤ በአውራጃዎችዋ ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።
[22] በእርስዋ ላይ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እርስዋን የሚበቀሉበት ጊዜዋ ነውና።
[23] ነገር ግን በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ በምድር ላይ ጽኑ መከራ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ መቅሠፍት ይሆናልና።
[24] በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ፤ በአሕዛብም ሁሉ ይማረካሉ፤ የአሕዛብ ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ ኢየሩሳሌምን ይረግጡአታል።
[25] “በፀሐይና በጨረቃ፥ በከዋክብትም ላይ ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ይጨነቃሉ፤ ከባሕሩና ከሞገዱ ድምፅ የተነሣም ይሸበራሉ።
[26] በዓለም ላይ ከሚመጣው ፍርሀትና ሽብር የተነሣም የሰዎች ነፍስ ትዝላለች፤ ያንጊዜ የሰማያት ኀይል ይናወጣልና።
[27] ያንጊዜም በሰማይ ደመና፥ በፍጹም ኀይልና ክብር ሲመጣ የሰውን ልጅ ያዩታል።
[28] ይህም ሁሉ በሆነ ጊዜ ወደ ላይ አቅንታችሁ ተመልከቱ፤ ራሳችሁንም አንሡ፤ የሚያድናችሁ መጥቶአልና።”
[29] ምሳሌም መስሎ እንዲህ አላቸው ፥ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ።
[30] ለምልመውም ያያችኋቸው እንደ ሆነ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ።
[31] እንዲሁ እናንተም ይህ እንደ ሆነ ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ደረሰች ዕወቁ።
[32] እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪደረግ ድረስ ይህቺ ትውልድ አታልፍም።
[33] ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ቃሌ ግን አያልፍም።
[34] “ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፥ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች።
[35] በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ተዘረጋች ወጥመድ ትደርሳለችና።
[36] እንግዲህ ከዚህ ከሚመጣው ሁሉ በጸሎታችሁ ማምለጥ እንድትችሉ፥ በሰው ልጅ ፊትም እንድትቆሙ ሁልጊዜ ትጉ።”
[37] ቀን ቀን በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ወጥቶ ደብረ ዘይት በሚባለው ተራራ ያድር ነበር።
[38] ሕዝቡም ሁሉ ቃሉን ሊሰሙ እርሱ ወዳለበት ወደ መቅደስ ማልደው ይሄዱ ነበር።