Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:38

[1] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢያሪኮ ገብቶ በዚያ ያልፍ ነበር።

[2] እነሆ፥ የቀራጮች አለቃ ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ባለጸጋ ነበር።

[3] ጌታችን ኢየሱስንም ያየው ዘንድ፥ ማን እንደ ሆነም ያውቅ ዘንድ ይሻ ነበር፤ የሰው ብዛትም ይከለክለው ነበር፤ ቁመቱ አጭር ነበርና።

[4] ወደ ፊቱም ሮጠ፤ ያየው ዘንድም በሾላ ላይ ወጣ፤ በዚያች መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና።

[5] ጌታችን ኢየሱስም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ አሻቅቦ አየውና ፥ “ዘኬዎስ ሆይ፥ ፈጥነህ ውረድ፤ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ አለኝና ” አለው።

[6] ፈጥኖም ወረደ፤ ደስ እያለውም ወደ ቤቱ ይዞት ገባ።

[7] ሁሉም አይተው “ወደ ኀጢኣተኛ ሰው ቤት ሊውል ገባ ” ብለው አንጐራጐሩ።

[8] ዘኬዎስም ቆመና ጌታችንን እንዲህ አለው ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አሁን የገንዘቤን እኩሌታ ለነዳያን እሰጣለሁ፤ የበደልሁትም ቢኖር ስለ አንድ ፋንታ አራት እጥፍ እከፍለዋለሁ።”

[9] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ዛሬ ለዚህ ቤት ሕይወት ሆነ፤ እርሱ የአብርሃም ልጅ ነውና።

[10] የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና።”

[11] ይህንም ሲሰሙ፤ ምሳሌ መስሎ ነገራቸው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ነበርና፤ እነርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ወዲያውኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበርና።

[12] እንዲህም አለ ፥ “አንድ የከበረ ሰው መንግሥት ይዞ ሊመለስ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ።

[13] ዐሥሩን አገልጋዮቹንም ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ፥ እንግዲህ እስክመለስ ድረስ ነግዱ አላቸው።

[14] የሀገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና፥ ይህ በእኛ ላይ ሊነግሥ አንሻም ብለው አከታትለው መልእክተኟችን ላኩ።

[15] ከዚህም በኋላ፤ መንግሥትን ይዞ በተመለሰ ጊዜ እንደ አተረፉ ያውቅ ዘንድ ምናን የሰጣቸውን ብላቴኖቹን እንዲያመጡአቸው አዘዘ።

[16] አንደኛውም መጥቶ ፥ አቤቱ፥ ምናንህ ዐሥር ነበር፤ እነሆ ዐሥር ምናን አትርፌአለሁ አለው።

[17] ጌታውም ፥ መልካም፥ አንተ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለሆንህ በብዙ ላይ እሾምሃለሁ፤ በዐሥሩ ከተሞች ላይ ተሾም አለው።

[18] ሁለተኛውም መጥቶ ፥ አቤቱ፥ ምናንህ አምስት ነበር፤ አምስት አትርፌአለሁ አለው።

[19] እርሱንም ፥ አንተም በአምስት ከተሞች ተሾም አለው።

[20] ሦስተኛውም መጥቶ እንዲህ አለው ፥ አቤቱ፥ በእኔ ዘንድ የነበረቺው ምናንህ እነኋት፤ በጨርቅ ጠቅልዬ አኑሬአት ነበር።

[21] አንተ ያላኖርኸውን የምትወስድ፥ ያልዘራኸውን የምታጭድ፥ ያልበተንኸውንም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ ስለማውቅህ ፈርቼሃለሁና።

[22] ጌታውም እንዲህ አለው ፥ አንተ ክፉ ሰነፍ አገልጋይ፥ እኔ ያላስቀመጥሁትን የምወስድ፥ ያልዘራሁትን የማጭድ፥ ያልበተንሁትንም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? እንደ ቃልህ እፈርድብሃለሁ።

[23] ለምን ገንዘቤን ወደ ለዋጮች አላስገባህም? እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር በወሰድሁት ነበር።

[24] ከዚያ የቆሙትንም ፥ ይህን ምናን ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር ምናን ላለው ስጡት አላቸው።

[25] እነርሱም አቤቱ፥ ዐሥር ምናን ያለው አይደለምን? አሉት።

[26] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ ላለው ሁሉ ይሰጡታል፤ ይጨምሩለታልም፤ የሌለውን ግን ያን ያለውንም ቢሆን ይወስዱበታል።

[27] ነገር ግን እነዚያን ልነግሥባቸው ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ውጉአቸው።”

[28] ይህንም ተናግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ወጣ።

[29] ደብረ ዘይት ወደሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ።

[30] እንዲህም አላቸው ፥ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ገብታችሁም ሰው ያልተቀመጠበት የታሰረ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ።

[31] ለምን ትፈቱታላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ።”

[32] የተላኩትም ሄደው እንደ አላቸው አገኙ።

[33] ውርንጫውንም ሲፈቱ ባለቤቶቹ “ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው።

[34] እነርሱም “ጌታው ይሻዋል ” አሉ።

[35] ይዘውም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱት፤ በውርንጫው ላይም ልብሳቸውን ጭነው ጌታችን ኢየሱስን በዚያ ላይ አስቀመጡት።

[36] ሲሄዱም በመንገድ ልብሳቸውን አነጠፉ።

[37] ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት መውረጃም በደረሱ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ስለ አዩት ኀይል ሁሉ ደስ ይላቸውና እግዚአብሔርን በታላቅ ቃል ያመሰግኑት ዘንድ ጀመሩ።

[38] እንዲህ እያሉ ፥ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ የእስራኤል ንጉሥ ቡሩክ ነው፤ ሰላም በምድር፥ በአርያምም ክብር ይሁን።”

[39] ከፈሪሳውያንም በሕዝቡ መካከል ፥ “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው ” ያሉት ነበሩ።

[40] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እነዚህ ዝም ቢሉ እኒህ ድንጋዮች ይጮሀሉ።”

[41] በደረሰ ጊዜም ከተማዪቱን አይቶ አለቀሰላት።

[42] እንዲህም አላት ፥ “አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበረ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ።

[43] ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል።

[44] አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይንም በደንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና።”

[45] ወደ ቤተ መቅደስም ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የለዋጮችንም መደርደሪያ፥ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ።

[46] “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል የሚል ጽሑፍ አለ፤ እናንተ ግን የሌቦችና የቀማኟች ዋሻ አደረጋችሁት ” አላቸው።

[47] ዘወትርም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝብ ታላላቆችም ሊገድሉት ይሹ ነበር።

[48] ነገር ግን የሚያደርጉትን አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ትምህርቱን በመስማት ይመሰጡ ነበርና።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters