[1] ጌታችን ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስን ተመልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ መንፈስም ወደ ምድረ በዳ ወሰደው።
[2] አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከዲያብሎስ ተፈተነ፥ በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ እነዚያም ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ተራበ።
[3] ዲያብሎስም ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ይህ ድንጋይ እንጀራ ይሁን በል ” አለው።
[4] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም የሚል ተጽፎአል ” አለው።
[5] ዲያብሎስም ወደ ረዥም ተራራ አወጣው፤ የዓለምን መንግሥታትም ሁሉ በቅፅበት አሳየው።
[6] ዲያብሎስም እንዲህ አለው ፥ “ይህን ሁሉ ግዛት፥ ይህንም ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥቶአልና፤ ለወደድሁትም እሰጠዋለሁና።
[7] ስለዚህ አንተ በፊቴ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ ለአንተ ይሁንልህ።”
[8] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ልትሰግድ፥ እርሱንም ብቻ ልታመልክ ተጽፎአል ” አለው።
[9] ወደ ኢየሩሳሌምም ወስዶ በቤተ መቅደሱ የማዕዘን ጫፍ ላይ አቆመው፤ እንዲህም አለው ፥ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ አንተ ራስህ ወደ ታች መር ብለህ ውረድ።
[10] በመንገድህ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል፤
[11] እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል ” ተብሎ ተጽፎአልና።
[12] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ” ተብሎአል አለው።
[13] ዲያብሎስም በዚህ ሁሉ እርሱን መፈታተኑን ከፈጸመ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ።
[14] ጌታችን ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመልሶ ወደ ገሊላ ሄደ፤ ዝናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማ።
[15] በየምኵuራባቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።
[16] ወደ አደገበት ወደ ናዝሬትም ሄደ፤ በሰንበት ቀንም እንዳስለመደ ወደ ምኵuራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ።
[17] የነቢዩን የኢሳይያስንም መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ እንዲህ የሚል የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።
[18] “የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥
[19] የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ።”
[20] መጽሐፉንም አጥፎ ለተላላኪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራብም የነበሩት ሁሉ ዐይናቸውን አትኲረው ተመለከቱት።
[21] እርሱም ፥ “የዚህ የመጽሐፍ ነገር ዛሬ በጆሮአችሁ ደረሰ፤ ተፈጸመም ” ይላቸው ጀመር።
[22] ሁሉም የንግግሩን መከናወን መሰከሩለት፤ የአንደበቱንም ቅልጥፍና እያደነቁ፥ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።
[23] እርሱም ፥ “በውኑ ባለ መድኀኒት ራስህን አድን፤ በቅፍርናሆም ያደረግኸውንና የሰማነውን ሁሉ በዚህም በሀገርህ ደግሞ አድርግ ብላችሁ ይህችን ምሳሌ ትመስሉብኛላችሁ ” አላቸው።
[24] እንዲህም አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በሀገሩ አይከብርም።
[25] እውነት እላችኋለሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን በምድር ሁሉ ብርቱ ረኃብ እስኪሆን ድረስ ሰማይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋበት ጊዜ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ።
[26] ኤልያስ የሲዶና ክፍል በምትሆን በስራጵታ ወደምትኖር ወደ አንዲት መበለት ሴት እንጂ ከእነዚህ ወደ አንዲቱ እንኳን አልተላከም።
[27] በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ አንድ እንኳን አልነጻም።”
[28] በምኵuራብም የነበሩት ሁሉ ይህን ሰምተው ተቈጡ።
[29] ያንጊዜም ተነሥተው ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፤ ገፍተውም ይጥሉት ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ተራራ ጫፍ ወሰዱት።
[30] እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
[31] ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር።
[32] አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ ነበር።
[33] በምኵuራብም ርኩስ መንፈስ የያዘው አንድ ሰው ነበር፤ በታላቅ ቃልም ጮኾ ፥
[34] “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ያለጊዜአችን ልታጠፋን መጣህን? የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ፥ አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቅሃለሁ ” አለ።
[35] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ዝም በልና ከእርሱ ውጣ ” ብሎ ገሠጸው፤ ጋኔኑም በምኵuራቡ መካከል ጣለውና ከእርሱ ወጣ፤ ነገር ግን ምንም አልጐዳውም።
[36] ሁሉም ደነገጡ፤ እርስ በርሳቸውም ተነጋገሩ፤ እንዲህም አሉ ፥ “ይህ ነገር ምንድን ነው? ክፉዎችን አጋንንት በሥልጣንና በኀይል ያዝዛቸዋልና፥ እነርሱም ይወጣሉና።”
[37] ዝናውም በዙሪያዉ ባሉ መንደሮች ሁሉ ወጣ፤ ተሰማም።
[38] ከምኵuራቡም ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ፤ የስምዖን አማትም በብርቱ ንዳድ ታማ ነበርና ስለ እርስዋ ነገሩት።
[39] በአጠገብዋም ቁሞ ንዳድዋን ገሠጸውና ተዋት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው።
[40] ፀሐይም በገባ ጊዜ ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸውን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ከእነርሱም በእያንዳንዱ ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።
[41] ብዙ አጋንንትም ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ” እያሉና እየጮሁ ይወጡ ነበር፤ እርሱም ይገሥጻቸው ነበር፤ ክርስቶስም እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና እንዲናገሩ አይፈቅድላቸውም ነበር።
[42] በነጋ ጊዜም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም እየፈለጉት ወደ እርሱ ሄዱ፤ አልፎአቸው እንዳይሄድም አቆሙት።
[43] እርሱ ግን ፥ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎች ከተሞች ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እነግራቸው ዘንድ ይገባኛል ” አላቸው።
[44] በገሊላ ምኲራቦችም ይሰብክ ነበር።