[1] ከዚህም በኋላ ጌታችን ሌሎች ሰባ ሰዎችን መረጠ፤ ሁለት ሁለት አድርጎም ሊሄድበት ወደ አለው ከተማና መንደር በፊቱ ላካቸው።
[2] ጌታችን ኢየሱስም አላቸው ፥ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው፤ እንግዲህ ለመከሩ ሠራተኛ ጨምሮ ይልክ ዘንድ ባለ መከሩን ለምኑት።
[3] ሂዱ፤ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵuላዎች መካከል እልካችኋለሁ።
[4] ከረጢትም፥ ስልቻም፥ ጫማም፥ ምንም ምን አትያዙ፤ በመንገድም ማንንም ሰላም አትበሉ።
[5] ወደ ገባችሁበት ቤትም አስቀድማችሁ ‘ለዚህ ቤት ሰዎች ሰላም ይሁን ’ በሉ።
[6] በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ ያለዚያ ግን ሰላማችሁ ይመለስላችኋል።
[7] በዚያም ቤት ተቀመጡ፤ ከእነርሱ የተገኘውንም ብሉ፥ ጠጡም፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና፤ ከቤትም ወደ ቤት አትሂዱ።
[8] ወደ ማናቸውም ከተማ ብትገቡ፥ የዚያ ከተማ ሰዎችም ቢቀበሉአችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ።
[9] በውስጥዋ የሚገኙትን ድውያንንም ፈውሱ፤ ‘የእግዚአብሔርም መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች ’ በሉአቸው።
[10] ነገር ግን ወደ ማናቸውም ከተማ ብትገቡ፥ የዚያች ከተማ ሰዎችም ባይቀበሉአችሁ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። እንዲህም በሉ ፥
[11] ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን ዕወቁ።
[12] በፍርድ ቀን ሰዶም ከዚያች ከተማ ይልቅ እንደምትሻል ይቅርታንም እንደምታገኝ እነግራችኋለሁ።
[13] “ኮራዚ ወዮልሽ! ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ቀድሞ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው በተቀመጡ ንስሓም በገቡ ነበር።
[14] ነገር ግን ጢሮስና ሲዶና ከእናንተ ይልቅ በፍርድ ቀን ይቅርታን ያገኛሉ።
[15] አንቺም ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ።
[16] “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም እንቢ የሚል እኔን እንቢ ይላል፤ እኔንም እንቢ የሚል የላከኝን እንቢ ይላል፤ እኔንም የሚሰማ የላከኝን ይሰማል።”
[17] እነዚያም ሰባው ደስ ብሎአቸው ተመለሱና ፥ “አቤቱ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዙልን ” አሉት።
[18] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ሰይጣንን ከሰማይ እንደ መብረቅ ሲወድቅ አየሁት።
[19] እነሆ፥ ጊንጦችንና እባቦችን፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ ትረግጡ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋችሁ፤ የሚጐዳችሁም ነገር የለም።
[20] ነገር ግን አጋንንት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ግን ስማችሁ በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
[21] በዚያች ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ደስ አለው፤ እንዲህም አለ ፥ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከዐዋቂዎችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥኸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲሁ ሆኖአልና።
[22] ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ፤ ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር የሚያውቅ የለም። ወልድ ግን ለወደደው ይገልጥለታል።”
[23] ተመልሶም ደቀ መዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው።
[24] ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ፤ አላዩምም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ፥ አልሰሙም።”
[25] ከዚህ በኋላ አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ተነሣና ፥ “መምህር ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” አለው።
[26] እርሱም ፥ “በኦሪት ምን ተጽፎአል? እንዴትስ ታነብባለህ?” አለው።
[27] እርሱም መልሶ ፥ “እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ሰውነትህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ዐሳብህ ውደደው፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል ” አለው።
[28] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “መልካም መልሰሃል፤ እንዲሁ አድርግ፤ ትድናለህም ” አለው።
[29] ራሱን ሊያከብር ባልንጀራውንም ሊንቅ ወድዶ ፥ “ባልንጀራዬ ማነው?” አለው።
[30] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ ነበር፤ ሽፍቶችም አገኙት፤ ደበደቡት፥ አቈሰሉት፥ ልብሱንም ገፍፈው፤ በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ።
[31] አንድ ካህንም በዚያች መንገድ ሲወርድ ድንገት አገኘው፤ አይቶም አልፎት ሄደ።
[32] እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገኘውና፥ አይቶ እንደ ፊተኛው አልፎት ሄደ።
[33] አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት።
[34] ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቐስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቐስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ።
[35] በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና ፥ ‘በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ ’ አለው።
[36] እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል?”
[37] እርሱም“ምሕረት ያደረገለት ነዋ ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ ” አለው።
[38] ከዚህም በኋላ ሄደው ወደ አንዲት መንደር ገቡ፤ ማርታ የምትባል አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው።
[39] ማርያም የምትባል እኅትም ነበረቻት፤ እርስዋም ከጌታችን ኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ትምህርቱን ትሰማ ነበር።
[40] ማርታ ግን ብዙ በማዘጋጀት ትደክም ነበር፤ ቆማም ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እኅቴ ትታኝ ብቻዬን ስሠራ አያሳዝንህምን? ርጃት በላት ” አለችው።
[41] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት ፥ “ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትደክሚያለሽ፥ ትቸገሪያለሽም፤ ታዘጋጂያለሽም።
[42] ጥቂት ይበቃል፤ ያም ባይሆን አንድ ይበቃል፤ ማርያምስ የማይቀሙአትን መልካም ዕድል መረጠች።”