Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:42

[1] ሁሉም በሙሉ ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት።

[2] እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር ፥ “ይህ ሰው ለቄሣር ግብር እንዳይሰጡ ሲከለክልና ሕዝቡን ሲያሳምፅ፥ ራሱንም የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስን ሲያደርግ አገኘነው።”

[3] ጲላጦስም ፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እኔ እንደ ሆንሁ አንተ አልህ ” አለው።

[4] ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ፥ “በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንድስ እንኳ በደል የለም ” አላቸው።

[5] ሕዝቡም ፥ “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል ” እያሉ አጽንተው ጮኹ።

[6] ጲላጦስም “ገሊላ ” ሲሉ ሰምቶ፤ ሰውየዉ ገሊላዊ እንደ ሆነ የገሊላን ሰዎች ጠየቀ።

[7] ከሄሮድስ ግዛትም ውስጥ መሆኑን ዐውቆ ወደ ሄሮድስ ላከው፤ ሄሮድስ በዚያ ወራት በኢየሩሳሌም ነበርና።

[8] ሄሮድስም ጌታችን ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ዜናውን ስለሚሰማ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይሻ ነበርና፤ የሚያደርገውንም ተአምራት ሊያይ ይመኝ ነበርና።

[9] በብዙ ነገርም መረመረው፤ እርሱ ግን አንድስ እንኳ አልመለሰለትም።

[10] የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር።

[11] ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር አቃለለው፤ አፌዘበትም፤ የሚያንፀባርቅ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው።

[12] በዚያም ቀን ሄሮድስና ጲላጦስ ተስማሙ፤ ቀድሞ ጥል ነበራቸውና።

[13] ጲላጦስም የካህናት አለቆችንና መኳንንቱን፥ ሕዝቡንም ጠራቸው።

[14] እንዲህም አላቸው ፥ “ይህን ሰው ሕዝብን ያሳምፃል ብላችሁ ወደ እኔ አመጣችሁት፤ በፊታችሁም እነሆ፥ መረመርሁት፤ ግን እናንተ ካቀረባችሁት ክስ በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንዳች በደል የለም።

[15] ወደ ሄሮድስም ሰድጃችሁ ነበር፤ እርሱም ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ ለሞትም የሚያበቃ ያደረገው ነገር የለም።

[16] እነሆ፥ እኔም እንግዲህ ገርፌ ልተወው ” አለ።

[17] በየበዓሉም ከእስረኟች አንድ ሊፈታላቸው ልማድ ነበር።

[18] ሁሉም በሙሉ ፥ “ይህን አስወግደው፥ ስቀለውም፥ በርባንን ግን ፍታልን ” ብለው ጮሁ።

[19] ያ በርባን ግን በከተማ ሁከት ያደረገና ነፍስ በመግደል የታሰረ ነበር።

[20] ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ወድዶ ፥ “ ኢየሱስን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” ብሎ እንደ ገና ተናገራቸው።

[21] እነርሱ ግን ፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮሁ ነበር።

[22] ጲላጦስም ለሦስተኛ ጊዜ ፥ “ምን ክፉ ነገር አደረገ? እነሆ፥ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት አላገኘሁበትም፤ እንኪያስ ልግረፈውና ልተወው ” አላቸው።

[23] እንዲሰቅሉትም ቃላቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ለመኑ፤ ጩኸታቸውና የካህናት አለቆች ድምፅም በረታ።

[24] ጲላጦስም የለመኑት ይሆንላቸው ዘንድ ፈረደበት።

[25] ያን የለመኑትን፥ ነፍስ በመግደልና ሁከት በማድረግ የታሰረውንም ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጣቸው።

[26] በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት።

[27] ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ።

[28] ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ።

[29] መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና።

[30] ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን ’ ይሉአቸዋል።

[31] በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?”

[32] ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ።

[33] ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ።

[34] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው ” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ።

[35] ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፤ አለቆችም ፥ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን ” እያሉ ያፌዙበት ነበር።

[36] ጭፍሮችም ይዘብቱበት ነበር፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ አመጡለት።

[37] እንዲህም ይሉት ነበር ፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህስ ራስህን አድን።”

[38] በራስጌውም ደብዳቤ ጻፉ፤ ጽሕፈቱም በሮማይስጥ፥ በጽርዕና በዕብራይስጥ ሆኖ “የአይሁድ ንጉሣቸው ይህ ነው ” የሚል ነበር።

[39] አብረው ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ወንበዴ ፥ “አንተስ ክርስቶስ ከሆንህ ራስህን አድን፤ እኛንም አድነን ” ብሎ ተሳደበ።

[40] ጓደኛውም መልሶ ገሠጸው፤ እንዲህም አለው ፥ “አንተ በዚህ ፍርድ ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር አምላክህን አትፈራውምን?

[41] በእኛስ በሚገባ ተፈርዶብናል፤ እንደ ሥራችንም ፍዳችንን ተቀበልን፤ ይህ ግን ምንም የሠራው ክፉ ሥራ የለም።”

[42] ጌታችን ኢየሱስንም ፥ “አቤቱ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ ዐስበኝ ” አለው።

[43] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።”

[44] ቀትር በሆነ ጊዜም በስድስት ሰዓት ፀሐይ ጨለመ፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ።

[45] ፀሐዩም በጨለመ ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከመካከሉ ተቀደደ።

[46] ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ ፥ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ ” ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ።

[47] የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር አይቶ ፥ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው።

[48] ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

[49] የሚያውቁት ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉትም ሴቶች በሩቁ ቆመው ይህን ያዩ ነበር።

[50] እነሆ፥ በጎና ጻድቅ ሰው፥ የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው መጣ።

[51] እርሱም በአይሁድ በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ ሀገሩም የይሁዳ ዕጣ የሚሆን አርማትያስ ነበር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት ተስፋ ያደርግ ነበር።

[52] ወደ ጲላጦስም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ለመነ።

[53] ሥጋውንም አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ማንም ባልተቀበረበት፥ ከድንጋይም በተፈለፈለ መቃብር ቀበረው፤ ታላቅ ድንጋይም አንከባልሎ መቃብሩን ገጥሞ ሄደ።

[54] ያም ቀን የሰንበት መግቢያ ዐርብ ነበር።

[55] ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡ ሁለት ሴቶች ተከትለው፥ መቃብሩን፥ ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ዘይት አዘጋጁ፤ ነገር ግን በሰንበት አልሄዱም፤ ሕጋቸው እንዲህ ነበርና።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters