[1] ጌታችን ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው ፥ “መሰናክል ግድ ይመጣል፤ ነገር ግን መሰናክልን ለሚያመጣት ሰው ወዮለት።
[2] ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ አህያ የሚፈጭበት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም በተሻለው ነበር።
[3] ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወንድምህ አንተን ቢበድል ብቻህን ምከረው፤ ቢጸጸት ግን ይቅር በለው።
[4] በየቀኑ ሰባት ጊዜ ቢበድልም ሰባት ጊዜ ከተጸጸተ ይቅር በለው።”
[5] ሐዋርያትም ጌታን ፥ “እምነትን ጨምርልን ” አሉት።
[6] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ብትኖራችሁ ይህችን ሾላ ከሥርሽ ተነቅለሽ በባሕር ውስጥ ተተከዪ ብትሉአት ትታዘዝላችኋለች።”
[7] “አራሽ ወይም ከብት ጠባቂ አገልጋይ ያለው ከእናንተ ማን ነው? ከእርሻው በተመለሰ ጊዜ ጌታው ና፥ ፈጥነህ ወደዚህ ውጣና ከእኔ ጋር በማዕድ ተቀመጥ ይለዋልን?
[8] እራቴን አዘጋጅልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስም ታጥቀህ አሳልፍልኝ፤ ከዚህም በኋላ አንተ ብላ፥ ጠጣም ይለው የለምን?
[9] እንግዲህ ጌታው ያዘዘውን ሥራውን ቢሠራ ለዚያ አገልጋይ ምስጋና አለውን?
[10] እንዲሁ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ አድርጋችሁ ‘እኛ ሥራ ፈቶች አገልጋዮች ነን፤ ለመሥራትም የሚገባንን ሠራን ’ በሉ።”
[11] ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ።
[12] ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ።
[13] ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው ፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን ” አሉ።
[14] ባያቸውም ጊዜ ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ።
[15] ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ።
[16] በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር።
[17] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ?
[18] ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?”
[19] እርሱንም ፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ ” አለው።
[20] ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም።
[21] እንኋት፥ በዚህ ናት፤ ወይም እነኋት፥ በዚያ ናት አይሉአትም፤ የእግዚአብሔር መንግሥትስ እነኋት፥ በመካከላችሁ ናት።”
[22] ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው ፥ “ከሰው ልጆች ቀኖች አንዲቱን ታዩ ዘንድ የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩአትም።
[23] እነሆ፥ በዚህ ነው፥ ወይም እነሆ፥ በዚያ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ አትከተሉአቸውም።
[24] መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ እንደሚያበራ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነውና።
[25] ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ብዙ መከራን ይቀበላል፤ ይህች ትውልድም ትንቀዋለች፤ ትፈታተነዋለችም።
[26] በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል።
[27] ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ ነበረ፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን አንድ አድርጎ አጠፋ።
[28] በሎጥ ዘመንም ሲበሉና ሲጠጡ፥ ቤት ሲሠሩና ተክል ሲተክሉ፥ ሲሸጡና ሲገዙ ነበረ።
[29] ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነመ፤ ሁሉንም አጠፋ።
[30] የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ አይታወቅምም።
[31] ያንጊዜም በሰገነት ላይ ያለ፥ ገንዘቡም በምድር ቤት የሆነበት ሰው ለመውሰድ አይውረድ፤ በዱር ያለም ወደ ኋላው አይመለስ።
[32] የሎጥን ሚስት ዐስቡአት።
[33] ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚጥላትም ያድናታል።
[34] እላችኋለሁ ፥ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።
[35] ሁለት ሴቶችም በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ።
[36] ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።”
[37] እነርሱም መልሰው ፥ “አቤቱ፥ ወዴት ነው?” አሉት፤ እርሱም ፥ “ገደላ በአለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ ” አላቸው።