[1] ሰንበትም ባለፈች ጊዜ ማርያም መግደላዊት፥ የያዕቆብ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም መጥተው ሥጋዉን ሊቀቡ ሽቱ ገዙ።
[2] በእሑድ ሰንበትም እጅግ ማልደው ፀሐይ በወጣ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዱ።
[3] እርስ በርሳቸውም ፥ “ድንጋዪቱን ከመቃብሩ አፍ ላይ ማን ያነሣልናል?” አሉ፤ ድንጋዪቱ እጅግ ታላቅ ነበረችና።
[4] አሻቅበውም በተመለከቱ ጊዜ ደንጋዪቱ ተንከባልላ አዩ።
[5] ወደ መቃብሩም በገቡ ጊዜ አንድ ጐልማሳ ነጭ ልብስ ለብሶ በስተቀኝ ተቀምጦ አገኙና ደነገጡ።
[6] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትሻላችሁን? ተነሥቶአል፤ በዚህስ የለም፤ የተቀበረበትም ቦታ እነሆ።
[7] ነገር ግን፥ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስም ወደ ገሊላ እንደሚቀድማቸው ንገሩአቸው፤ እንደ ነገራቸውም በዚያ ያዩታል።”
[8] ከመቃብርም ወጥተው ሸሹ፤ ፍርሀትና ድንጋጤ ይዞአቸዋልና፤ ስለ ፈሩም ለማንም አልተናገሩም፤ ያዘዛቸውንም ሁሉ ለጴጥሮስና ለወንድሞቹ ተናገሩ። ጌታችን ኢየሱስም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ተገለጠላቸውና፥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን የማይለወጥ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረቱ ሁሉ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይሰብኩ ዘንድ ላካቸው።
[9] በእሑድ ሰንበትም ማለዳ ተነሥቶ ሰባት አጋንንትን ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት አስቀድሞ ታያት።
[10] እርስዋም ሄዳ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ ነገረቻቸው።
[11] እነርሱ ግን ሕያው እንደ ሆነ፥ ለእርስዋም እንደ ተገለጠላት በሰሙ ጊዜ አላመንዋትም።
[12] ከዚህም በኋላ፥ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ተገለጠላቸው።
[13] እነርሱም ደግሞ ሄደው ለባልንጀሮቻቸው ነገሩ፤ እነርሱንም ቢሆን አላመኑአቸውም።
[14] ከዚህም በኋላ፥ ደግሞ ዐሥራ አንዱ በማዕድ ተቀምጠው ሳለ ተገለጠላቸው፤ እንደ ተነሣ ያዩትን አላመኑአቸውምና ስለ ሃይማኖታቸው ጕuድለት ገሠጻቸው፤ የልባቸውንም ጽናት ነቀፈ።
[15] እንዲህም አላቸው ፥ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ።
[16] ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።
[17] ይህችም ምልክት በስሜ የሚያምኑትን ትከተላቸዋለች፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቌንቌም ይናገራሉ።
[18] እባቦችንም በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚጐዳቸውም ነገር የለም፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡም የሚጐዳቸው የለም፤ በድውያን ላይም እጃቸውን ይጭናሉ፤ ድውያኑም ይፈወሳሉ።”
[19] ጌታችን ኢየሱስም ከተነጋገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ።
[20] እነርሱም ወጥተው ጌታ እየረዳቸው፥ ቃሉንም በማያቌርጥ ተአምር እያጸናላቸው በስፍራው ሁሉ አስተማሩ። ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ወንጌላዊው ማርቆስ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ፤ የጻፈውም በሮም ሀገር በሮማይስጥ ቌንቌ፤ ጌታችን በሥጋ ወደ ሰማይ ባረገ በዐሥራ አንድ ዓመት፥ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በአራት ዓመት ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።