[1] ዳግመኛም ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ገባ፤ በቤትም እንዳለ ተሰማ።
[2] በደጅ ያለው ቦታም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙዎች ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ወደ እርሱ ለመጡትም ቃሉን ይነግራቸው ነበር።
[3] አራት ሰዎችም ሽባ የሆነ በሽተኛን በአልጋ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡለት።
[4] ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢሳናቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ ነድለው ሽባዉን ከነአልጋው አወረዱት።
[5] ጌታችን ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ያን ሽባ ፥ “ልጄ ሆይ ኀጢአትህ ተሰረየልህ ” አለው።
[6] በዚያም ጻፎች ተቀምጠው ነበሩ፤ በልባቸውም ዐሰቡ።
[7] “ይህ ስለምን እንዲህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንድ ከእግዚአብሔር በቀርስ ኀጢአትን ማስተስረይ ማን ይችላል?” አሉ።
[8] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ እንደሚያስቡ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው ፥ “በልባችሁ እንዲህ ያለ ነገር ለምን ታስባላችሁ?
[9] ይህን ሽባ ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና፤ ወይም ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
[10] ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥”
[11] ዳግመኛ ሽባውን ፥ “አንተን እልሃለሁ ተነሥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ግባ ” አለው።
[12] ያንጊዜም ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፤ ሁሉም አደነቁ፤ “እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
[13] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ባሕር ዳርቻ ዳግመኛ ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ሄዱና አስተማራቸው።
[14] ከዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አገኘውና ፥ “ተከተለኝ ” አለው፤ ተነሥቶም ተከተለው።
[15] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ በሌዊ ቤት በማዕድ ተቀመጠ፤ ብዙዎች ቀራጮችና ኀጢአተኟች ከጌታችን ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀምጠው ነበር፤ የተከተሉትም ብዙዎች ነበሩ።
[16] ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከኀጢአተኟችና ከቀራጮች ጋር ሲበላና ሲጠጣ አይተው፥ ደቀ መዛሙርቱን ፥ “መምህራችሁ ከኀጢአተኟችና ከቀራጮች ጋር ለምን ይበላል? ይጠጣልም?” አሉአቸው።
[17] ጌታችን ኢየሱስም በሰማ ጊዜ እንዲህ አላቸው ፥ “በሽተኟች ባለ መድኀኒትን ይሹታል፤ ጤነኟች ግን አይሹትም፤ ኀጥኣንን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።”
[18] የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑትም ይጿሙ ነበር፤ ሄደውም ፥ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ይጿማሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጿሙም?” አሉት።
[19] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጿም ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጿም አይችሉም።
[20] ነገር ግን፥ ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው የሚወስዱበት ቀን ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጿማሉ።
[21] በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢጣፍ ግን አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቀድደዋል፤ ቀዳዳውንም ያሰፋዋል።
[22] አዲስ የወይን ጠጅም በአሮጌ ረዋት የሚጨምር የለም፤ አዲሱ የወይን ጠጅ አሮጌውን ረዋት ይቀድደዋልና፤ ወይኑም ይፈስሳል፤ ረዋቱም ይቀደዳል፤ ነገር ግን፥ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ ረዋት ያደርጉታል።”
[23] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር በመንገድ ሲያልፉ እሸት ይቈርጡ ጀመር።
[24] ፈሪሳውያንም ፥ “ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ለምን ያደርጋሉ?” አሉት።
[25] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ዳዊት በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን አላነበባችሁምን?
[26] አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንደ ገባና ለካህናት ብቻ እንጂ እርሱ ሊበላው የማይገባውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ፥ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም እንደ ሰጣቸው አላነበባችሁምን?”
[27] ደግሞም እንዲህ አላቸው ፥ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጠረች እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም።
[28] እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው።”