Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 8:03

[1] ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ ሀገር ሄደ፤ ሕዝቡም ደግሞ ከእርሱ ጋር ሄዱ፤ እንደ አስለመደም ያስተምራቸው ነበር።

[2] ፈሪሳውያንም መጥተው ፥ “ለሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።

[3] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ሙሴ ምን አዘዛችሁ?” አላቸው።

[4] እነርሱም ፥ “ሙሴስ የምትፈታበትን ደብዳቤ ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ ” አሉት።

[5] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ስለ ልባችሁ ክፋት ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ሙሴ ይህን ትእዛዝ ሰጣችሁ።

[6] ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴትን ፈጠረ።

[7] ስለዚህም ወንድ አባትና እናቱን ትቶ ሚስቱን ይከተላታል።

[8] ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ፤ እንግዲያስ አንድ አካል ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም።

[9] እንግዲህ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ።”

[10] በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ ነገር ጠየቁት።

[11] እንዲህም አላቸው ፥ “ሚስቱን የሚፈታና ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል።

[12] እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።”

[13] ይባርካቸውም ዘንድ ሕፃናትን አመጡለት፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው።

[14] ጌታችን ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።

[15] እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ አይገባባትም።”

[16] አቀፋቸውም፤ እጁንም በራሳቸው ላይ ጭኖ ባረካቸው።

[17] በመንገድ ሲሄድም አንድ ሰው መጥቶ ሰገደለትና ፥ “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው።

[18] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም።

[19] ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።”

[20] እርሱም መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ ይህንስ ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ ” አለው።

[21] ጌታችን ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደው፤ “ፍጹም ልትሆን ብትወድስ አንዲት ነገር ቀርታሃለች፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለነዳያን ስጥ፤ በሰማያትም መዝገብ ታገኛለህ፤ የሞትህንም መስቀል ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ ” አለው።

[22] ስለዚህም ነገር ፊቱ ጠቈረ፤ ብዙ ንብረትም ነበረውና እያዘነ ሄደ።

[23] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘወር ብሎ ተመልክቶ ፥ “ገንዘብ ላለው ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?” አላቸው።

[24] ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር አደነቁ፤ ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው ፥ “ ልጆቼ ሆይ፥ በገንዘባቸው ለሚታመኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?

[25] ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።”

[26] እነርሱም እጅግ አድንቀው እርስ በርሳቸው ፥ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።

[27] ጌታችን ኢየሱስም አያቸውና ፥ “በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል ” አላቸው።

[28] ጴጥሮስም ፥ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ” ይለው ጀመር።

[29] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም እርሻን፥ ወይም ወንድሞችን፥ ወይም እኅቶችን፥ ወይም አባትን፥ ወይም እናትን፥ ወይም ሚስትን፥ ወይም ልጆችን የሚተው፥ በዚህ ዓለም በመከራና በስደት መቶ እጥፍ ቤትንና እርሻን፥ ወንድሞችንና እኅቶችን፥ አባትንና እናትን፥ ልጆችንም የማያገኝ የለም።

[30] በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል።

[31] ብዙዎች ፊተኟች ኋለኟችን ይሆናሉ፤ ኋለኟችም ፊተኟችን ይሆናሉ።”

[32] በመንገድም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጡ ጌታችን ኢየሱስ ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የሚከተሉትም ፈሩ፤ ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ወስዶ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር።

[33] እንዲህም አላቸው ፥ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የካህናት አለቆችና ጻፎችም የሰውን ልጅ ይይዙታል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።

[34] ያፌዙበታል፤ ይተፉበታልም፤ ይገርፉታልም፤ ይገድሉታልም፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”

[35] ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው ፥ “መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን እንድታደርግልን እንሻለን ” አሉት።

[36] እርሱም ፥ “ምን ላደርግላችሁ ትሻላችሁ?” አላቸው።

[37] እነርሱም ፥ “በጌትነትህ አንዳችን በቀኝህ፥ አንዳችንም በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን ” አሉት።

[38] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጿዕ ልትጠጡ ትችላላችሁን? እኔ የምጠመቀውን ጥምቀትስ ትጠመቃላችሁን?”

[39] እነርሱም ፥ “አዎን፥ እንችላለን ” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እኔ የምጠጣውንስ ጿዕ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቃትን ጥምቀትም ትጠመቃላችሁ።

[40] በቀኜና በግራዬ መቀመጥን ግን ሰማያዊ አባቴ ለሌሎች አዘጋጅቶላቸዋል እንጂ እኔ የምሰጣችሁ አይደለም።”

[41] ዐሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማቾች በያዕቆብና በዮሐንስ ተቈጡ።

[42] ጌታችን ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው ፥ “አሕዛብን አለቆቻቸው እንዲፈርዱባቸው፥ ታላላቆቻቸውም እንዲሠለጥኑባቸው አታውቁምን?

[43] ለእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ አለቃ ሊሆን የሚወድ አገልጋይ ይሁናችሁ።

[44] ከእናንተም ታላቅ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ታዛዥ ይሁናችሁ።

[45] የሰው ልጅ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ ሊያገለግሉት አልመጣምና።”

[46] ወደ ኢያሪኮም ገባ፤ ከኢያሪኮም በወጣ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ብዙ ሰውም ነበረ፤ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስም በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

[47] የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደ ሆነም ሰምቶ ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ ” ብሎ ጮኸ።

[48] ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አደረገና ፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ” አለ።

[49] ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ፥ “ጥሩት ” አለ፤ እነርሱም ዕውሩን ጠሩት፤ “በርታና ተነሥ፥ መምህር ይጠራሃል ” አሉት።

[50] እርሱም ተነሥቶ ልብሱን ትቶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ።

[51] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ምን ላደርግልህ ትሻለህ?” አለው፤ ዕውሩም ፥ “መምህር ሆይ፥ እንዳይ ነው ” አለው።

[52] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ ” አለው፤ ወዲያውም አየ፤ በመንገድም ተከተለው።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters