[1] ኢየሩሳሌም ለመግባት በደብረ ዘይት አጠገብ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በደረሱ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ።
[2] እንዲህም አላቸው ፥ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደርም በገባችሁ ጊዜ፥ ሰው በላዩ ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ።
[3] ‘ምን ታደርጋላችሁ?’ የሚላችሁ ሰው ቢኖርም ‘ጌታው ይሻዋል ’ በሉ፤ ወዲያውኑም ወደዚህ ይሰድደዋል።”
[4] ሄደውም በበሩ አጠገብ ባለው ሜዳ በመንገድ ዳር የታሰረ ውርንጫ አገኙ፤ ፈቱትም።
[5] ከዚያ ቆመው የነበሩትም ፥ “ምን ልታደርጉት ነው ውርንጫዉን የምትፈቱት?” አሉአቸው።
[6] ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸውም ነገሩአቸው፤ እነርሱም ተዉአቸው።
[7] ውርንጫዉንም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱና ልብሳቸውን በላዩ ደልድለው አስቀመጡት።
[8] ብዙዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።
[9] በፊት የሚሄዱ፥ በኋላም የሚከተሉ እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር ፥ “ሆሣዕና፥ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው።
[10] በእግዚአብሔር ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም።”
[11] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ ሁሉንም ተመልክቶ በመሸ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ሄደ።
[12] በነጋዉም ከቢታንያ በወጣ ጊዜ ተራበ።
[13] በለስንም ከሩቅ አየ፤ ቅጠልም ነበራት፤ በውስጥዋም የሚያገኘው ፍሬ እንዳለ ሊያይ ሄደ፤ ወደ እርስዋም በሄደ ጊዜ ከቅጠል ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትም፤ የበለስ ጊዜ አልነበረምና።
[14] መልሶም ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ከአንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር ” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱም ሰሙት።
[15] ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ያባርር ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ፥ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ።
[16] ማንም ዕቃ ተሸክሞ በመቅደስ እንዲያልፍ አልፈቀደም።
[17] “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎ የለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ” ብሎ አስተማራቸው።
[18] የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሰምተው የሚገድሉበትን ምክንያት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ትምህርቱን ያደንቁ ነበርና ፈሩት።
[19] በመሸም ጊዜ ከከተማ ወደ ውጭ ወጣ።
[20] በነጋዉም በተመለሱ ጊዜ ያቺን በለስ ከስርዋ ደርቃ አገኙአት።
[21] ጴጥሮስም ትዝ አለውና ፥ “መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ ያቺ የረገምሃት በለስ ደርቃለች ” አለው።
[22] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እግዚአብሔርን ማመን ይኑራችሁ፤
[23] እውነት እላችኋለሁ፥ ይህን ተራራ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት፥ በልባችሁም ባትጠራጠሩ፥ ብታምኑም እንደ ተናገራችሁት ይሆናል።
[24] ስለዚህ እላችኋለሁ፥ “አምናችሁ የምትጸልዩትንና የምትለምኑትንም ሁሉ ታገኛላችሁ፤ ይሆንላችሁማል።
[25] “በምትጸልዩበትም ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ።
[26] እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”
[27] ዳግመኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ በቤተ መቅደስም ሲመላለስ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጡ።
[28] “በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ? ወይስ ይህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት።
[29] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እኔም አንዲት ነገርን እጠይቃችኋለሁ፤ ንገሩኝ፤ እኔም በማን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።
[30] የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ነበረችን? ወይስ ከሰው? ንገሩኝ።”
[31] እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ ፥ “ከሰማይ ነው ብንለው እንኪያ ለምን አላመናችሁበትም? ይለናል።
[32] ከሰው ነው ብንለውም ሕዝቡን እንፈራለን፤” ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና።
[33] መልሰውም ለጌታችን ኢየሱስ ፥ “አናውቅም ” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “እኔም በማን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ አልነግራችሁም ” አላቸው።