Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:36

[1] በዚያም ወራት ደግሞ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም፤ ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤

[2] “እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ ሦስት ቀን ቈይተዋልና፤ የሚበሉትም የላቸውምና።

[3] እንደራባቸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ባሰናብታቸውም በመንገድ ይደክማሉ፤ ከእነርሱም መካከል ከሩቅ የመጡ አሉ።”

[4] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ይህን ሁሉ ሕዝብ በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ማጥገብ ማን ይችላል?” አሉት።

[5] እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ሰባት ” አሉት።

[6] ሕዝቡንም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤ ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም እንዲያ ቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሰዎች አቀረቡ።

[7] ጥቂት ዓሣም ነበራቸውና እርሱንም ባርኮ፥ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ።

[8] በልተውም ጠገቡ፤ ያነሡትም የተረፈው ቊርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሞላ።

[9] የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ፤ ከዚህም በኋላ አሰናበታቸው።

[10] ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በታንኳው ገብቶ ወደ ድልማኑታ አውራጃ ሄደ።

[11] ፈሪሳውያንም ወጥተው ይከራከሩት ጀመር፤ ሊፈታተኑትም ከሰማይ ምልክትን ጠየቁት።

[12] በልቡም አዝኖ ፥ “ይህች ትውልድ ምልክትን ለምን ትሻለች? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚች ትውልድ ምልክት አይሰጣትም ” አለ።

[13] ትቶአቸውም ደግሞ ወደ ታንኳ ገባ፤ ወደ ማዶም ሄደ።

[14] እንጀራ መያዝም ረስተው ነበርና በታንኳው ውስጥ ለእነርሱ ከአንዲት እንጀራ በቀር አልነበራቸውም።

[15] ጌታችንም ፥ “ዕወቁ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ” ብሎ አዘዛቸው።

[16] እነርሱም ፥ “እንጀራ አልያዝንምና እንዲህ ይለናል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።

[17] ጌታችን ኢየሱስም ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው ፥ “እንጀራ ስለሌላችሁ ለምን ታስባላችሁ? ገና አታውቁምን? ወይስ አታስተውሉምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን?

[18] ዐይን አላችሁ፥ አታዩምን? ጆሮም አላችሁ፥ አትሰሙምን? ወይስ አታስቡምን?

[19] አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ የተረፈውን ቐርስራሽ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ?” እነርሱም ፥ “ዐሥራ ሁለት ” አሉት።

[20] እርሱም ፥ “ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰው በቈረስሁ ጊዜ የተረፈውን ቐርስራሽ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “ሰባት ” አሉት።

[21] “እንግዲህ የማታስተውሉ ለምንድን ነው?” አላቸው።

[22] ወደ ቤተ ሳይዳም በደረሱ ጊዜ፥ አንድ ዕውር ሰው ወደ እርሱ አመጡ እንዲዳስሰውም ለመኑት።

[23] ያንም ዕውር በእጁ ይዞ ከመንደር አወጣው፤ በዐይኑ ላይም እንትፍ ብሎ ዳሰሰውና ፥ “ምን ታያለህ?” አለው።

[24] ተመልክቶም ፥ “ሰዎችን እንደ ዛፎች ወዲያና ወዲህ ሲመላለሱ አያለሁ ” አለ።

[25] ዳግመኛም ዐይኑን ዳሰሰውና አጥርቶ አየ፥ ዳነም፤ ብሩህም ሆኖለት ሁሉን ተመለከተ።

[26] “ወደ መንደር አትግባ፤ በመንደር ውስጥም ለማንም አንዳች አትናገር ” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

[27] ጌታችን ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በፊልጶስ ቂሣርያ ወደ አሉ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድም ፥ “ሰው እኔን ማን ይለኛል?” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።

[28] እነርሱም ፥ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል ” አሉት።

[29] “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ ጴጥሮስም ፥ “አንተ ክርስቶስ ነህ ” ብሎ መለሰለት።

[30] እርሱም ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።

[31] ሽማግሎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም የሰውን ልጅ ይነቅፉት ዘንድ ብዙ መከራም ያጸኑበት ዘንድ እንዳለው፥ እንደሚገድሉትና በሦስተኛው ቀንም እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።

[32] ይህንም ነገር በግልጥ ይነግራቸው ነበረ፤ ጴጥሮስም ቀርቦ ይከለክለው ጀመረ።

[33] ተመልሶም ወደ ደቀ መዛሙርቱ አየና ፥ “የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ ” ብሎ ጴጥሮስን ገሠጸው።

[34] ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።

[35] ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ያጠፋታል፤ ሰውነቱን ስለ እኔና ስለ ወንጌል የሚያጠፋትም ያገኛታል።

[36] ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?

[37] ሰው ለነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?

[38] በዚች አመንዝራና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍረውን ሁሉ፥ የሰው ልጅም በአባቱ ክብር ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ ያፍርበታል።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters