Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:28

[1] “እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት በኀይል ስትመጣ እስኪያዩአት ድረስ ሞትን የማይቀምሱት አሉ ” አላቸው።

[2] በስድስተኛውም ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸቸው ወደ ረዥም ተራራ አወጣቸው፤ መልኩም በፊታቸው ተለወጠ።

[3] ልብሱም አንጸባረቀ፤ ሸማ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ዓይነት አድርጎ ሊያነጻው እስከማይችል እጅግ ነጭ ሆነ።

[4] ሙሴና ኤልያስም ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገሩ ታዩአቸው።

[5] ጴጥሮስም መልሶ ጌታችን ኢየሱስን ፥ “መምህር ሆይ፥ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ሦስት ዳስም እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ ” አለው።

[6] ደንግጠው ነበርና የሚናገረውን አያውቅም ነበር።

[7] ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት ” የሚል ቃል መጣ።

[8] ከዚህም በኋላ ድንገት ዙሪያውን በተመለከቱ ጊዜ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ብቻ በቀር ሌላ ከእነርሱ ጋር ያዩት የለም።

[9] ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን ተለይቶ እስኪነሣ ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።

[10] ቃሉንም ይዘው ፥ “ከሙታን ተለይቶ መነሣት ምንድን ነው?” ብለው እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።

[11] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ጻፎች፥ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት።

[12] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፤ እንኪያ ብዙ መከራ እንደሚያጸኑበት፥ እንደሚንቁትም ስለ ሰው ልጅ እንዴት ተብሎ ተጻፈ?

[13] ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ በእርግጥ መጥቶአል፤ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈም የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት።”

[14] ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ፥ ብዙ ሰዎች ከብበዋቸው፥ ጻፎችም ሲከራከሩአቸው አገኘ።

[15] ሰዎችም ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፤ ወዲያውም ወደ እርሱ ሮጡና እጅ ነሡት።

[16] ጻፎችንም ፥ “ስለምን ትከራከሩአቸዋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።

[17] ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው መልሶ እንዲህ አለ ፥ “መምህር ሆይ፥ ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ ዲዳ ጋኔን ይዞታልና።

[18] ባገኘበትም ቦታ ይጥለዋል፤ ያፈራግጠዋል፤ አረፋ ያስደፍቀዋል፤ ጥርሱንም ያፋጨዋል፤ ያደርቀዋል፤ ለደቀ መዛሙርትህም ያወጡለት ዘንድ ነገርኋቸው፤ ነገር ግን መፈወስ ተሳናቸው።

[19] እርሱም መልሶ ፥ “እምነት የሌላት ትውልድ፥ እስከ መቼ ድረስ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼ ድረስስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት ” አላቸው።

[20] ወደ እርሱም ወሰዱት፤ ያም ጋኔን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ በመሬት ላይ ጣለው፤ አፈራገጠው፤ አረፋም አስደፈቀው።

[21] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “የያዘው ከመቼ ጀምሮ ነው?” ብሎ አባቱን ጠየቀው፤ እርሱም ፥ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው።

[22] ብዙ ጊዜ ሊገድለው ወደ ገደል ወደ እሳትም ወደ ውኃም ይጥለዋል፤ ነገር ግን ቢቻልህ እዘንልኝ፤ ርዳኝም ” አለው።

[23] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ቢቻልህ ብለሃል፤ ብታምንስ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ” አለው።

[24] የዚያ ብላቴና አባትም ፥ “አቤቱ፥ አምናለሁ፤ ነገር ግን አለማመኔን ርዳው ” ብሎ ጮኸ።

[25] ጌታችን ኢየሱስም ሰው ሲራወጥ አይቶ “አንተ ዲዳ፥ ደንቆሮም ጋኔን ከእርሱ እንድትወጣ፥ ዳግመኛም እንዳትመለስበት እኔ አዝዤሃለሁ ” ብሎ ያን ክፉ ጋኔን ገሠጸው።

[26] ጮኾም እጅግ አፈራገጠውና ወጣ፤ ብዙዎችም ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ በድን ሆነ።

[27] ጌታችን ኢየሱስም በእጁ ይዞ አስነሣው፥ ቆመም።

[28] ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ሆነው ፥ “ስለምን እኛ እርሱን ማውጣት ተሳነን?” አሉት።

[29] እርሱም ፥ “ይህ ወገን ያለ ጿምና ያለ ጸሎት ሊወጣ አይችልም ” አላቸው።

[30] ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ማንም ያውቀው ዘንድ አልፈቀደም።

[31] “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይገድሉታልም፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል ” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተምራቸው ነበርና።

[32] የነገራቸውንም አላስተዋሉም፤ ሊጠይቁትም ይፈሩ ነበር።

[33] ወደ ቅፍርናሆም ደርሶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ፥ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ትነጋገሩ ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው።

[34] በመንገድ እርስ በርሳቸው ፥ “ ከእነርሱ ማን ይበልጣል?” ተባብለው ነበርና ዝም አሉ።

[35] ተቀምጦም ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ ፥ “አለቃ ሊሆን የሚወድ ራሱን ለሁሉ ዝቅ ያድርግ፤ ለሁሉም አገልጋይ ይሁን ” አላቸው።

[36] ሕፃንንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው፤ አቅፎም እንዲህ አላቸው ፥

[37] “እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝንም እንጂ እኔን ብቻ የሚቀበል አይደለም።”

[38] ዮሐንስም መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ ያየነው አንድ ሰው አለ፤ ከእኛም ጋር ስላልተከተለህ ከለከልነው ” አለው።

[39] ጌታችን ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው ፥ “በስሜ ተአምራትን የሚያደርግ፥ ወዲያውም በእኔ ላይ ክፉ ቃልን ሊናገር የሚችል የለምና አትከልክሉት።

[40] ባላጋራችሁ ካልሆነ ባልንጀራችሁ ነውና።

[41] እናንተ የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ፥ በስሜ ቀዝቃዛ ጿ ውኃ የሚያጠጣችሁ ዋጋውን እንደማያጣ እውነት እላችኋለሁ።

[42] “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን የሚያስት አህያ የሚፈጭበት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል።

[43] እጅህም ብታስትህ ቊረጣት፤ ጕuንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና።

[44] ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት፥ ትሉም ወደማያንቀላፋበት ወደ ገሃነም እሳት ከምትገባ፥

[45] እግርህም ብታስትህ ቐረጣት፤ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና።

[46] ሁለት እግር ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት፥ ትሉም ወደማያንቀላፋበት ወደ ገሃነም እሳት ከምትገባ።

[47] ዐይንህም ብታስትህ አውጣት፤ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ብትገባ ይሻልሃልና።

[48] ሁለት ዐይን ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት፥ ትሉም ወደማያንቀላፋበት ወደ ገሃነም እሳት ከምትገባ።

[49] “ሁሉም በእሳት ይጣፍጣልና መሥዋዕት ሁሉ በጨው ይጣፍጣል።

[50] ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በውስጣችሁ ጨው ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters