Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:09

[1] ምሳሌም ይመስልላቸው ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም አስቈፈረለት፤ በውስጡም ግንብ ሠራ፥ ለገባሮችም ሰጥቶ ወደ ሌላ ሀገር ሄደ።

[2] በጊዜውም ከወይኑ ፍሬ ያመጣለት ዘንድ ወደ ገባሮች አገልጋዩን ላከ።

[3] ይዘውም ገረፉት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።

[4] ዳግመኛም ሌላዉን አገልጋዩን ወደ እነርሱ ላከ፤ እርሱንም ደበደቡት፤ ቀጥቅጠውና አዋርደውም ሰደዱት።

[5] እንደገናም ሌላዉን አገልጋዩን ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፤ ሌሎችንም ብዙዎች አገልጋዮችን ላከ፤ የገረፉትም አለ፤ የገደሉትም አለ።

[6] የሚወደውም አንድ ልጅ ነበረው፤ ከሁሉም በኋላ ‘ልጄንስ ያፍሩታል ’ ብሎ ወደ እነርሱ ላከው።

[7] ገባሮችም ፥ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እጅ እናድርግ ’ አሉ።

[8] ይዘውም ከወይኑ ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።

[9] እንግዲህ የወይኑ ባለቤት ምን ያደርጋቸው ይሆን? መጥቶ እነዚያን ገባሮች ያጠፋቸዋል፤ ወይኑንም ለሌሎች ይሰጣል።

[10] ይህንስ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ‘ግንበኟች የናቁአት ድንጋይ እርስዋ የማዕዘን ራስ ሆነች።

[11] እርስዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ናት’።”

[12] ይህንም ምሳሌ ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ ዐውቀዋልና ሊይዙት ወደዱ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ፤ ትተውትም ሄዱ።

[13] ፈሪሳውያንም በቃሉ ያስቱት ዘንድ ሰዎችን ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ወደ እርሱ ላኩ።

[14] እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት ፥ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ እንደ ሆንህ እናውቃለን፤ ማንም አያሳዝንህም፤ የሰው ፊትም አይተህ አታዳላም፤ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህና ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባልን? ወይስ አይገባም? እንስጥን? ወይስ አንስጥ?”

[15] ጌታችን ኢየሱስም ተንኰላቸውን ዐወቀባቸውና ፥ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ገንዘቡን አምጥታችሁ አሳዩኝ ” አላቸው።

[16] እነርሱም አመጡለት፤ “ይህ መልኩ፥ ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም “የቄሣር ነው ” አሉት።

[17] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “የቄሣርን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አድርጉ ” አላቸው፤ አደነቁትም።

[18] ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጡ።

[19] እንዲህም ብለው ጠየቁት ፥ “መምህር ሆይ፥ የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይኖረው ሚስቱን ትቶ ቢሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ሙሴ ጽፎልን ነበር።

[20] እንግዲህ በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ታላቁ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ።

[21] ሁለተኛዉም አገባትና ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛዉም እንዲሁ።

[22] ሰባቱም አገቡአት፤ ዘርም አልተዉም፤ ከሁሉም በኋላ ያቺ ሴት ሞተች።

[23] እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ከእነርሱ ለማንኛው ሚስት ትሆናለች? ሰባቱም አግብተዋት ነበርና።”

[24] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቅ ተሳሳታችሁ።

[25] ሙታንስ በሚነሡበት ጊዜ እነርሱ በሰማያት እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆነው ይኖራሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም።

[26] ሙታን እንዲነሡ ግን እግዚአብሔር በዕፀ ጳጦስ ዘንድ ‘እኔ እግዚአብሔር የአንተ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ’ ብሎ የነገረውን በሙሴ መጽሐፍ አላነበባችሁምን?

[27] እንግዲህ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ እናንተ ግን በብዙ ትሳሳታላችሁ።”

[28] ከጸሓፊዎችም አንዱ ፥ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማና መልካም እንደ መለሰላቸው አይቶ ፥ “ከሁሉ የምትበልጠው ትእዛዝ የትኛይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው።

[29] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ የምትበልጠው ይህች ናት፤ ‘እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ነው።

[30] እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ዐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፤’ የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

[31] የምትመስላትም ሁለተኛይቱ ይህቺ ናት፤ ‘ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ ’ ከእነዚህ ከሁለቱ ትእዛዛት የሚበልጥ የለም።”

[32] ያም ጸሓፊ እንዲህ አለው ፥ “መምህር ሆይ፥ በእውነት መልካም ብለሃል፤ እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ የለም።

[33] በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ዐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስ መውደድ ከመባና ከመሥዋዕት ሁሉ ይበልጣል።”

[34] ጌታችን ኢየሱስም ብልህ እንደ ሆነ አይቶ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም ” አለው፤ ከዚህ በኋላ ግን ሊጠይቀው የደፈረ የለም።

[35] ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ሲያስተምራቸው እንዲህ አላቸው ፥ “ጸሓፊዎች ፥ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?

[36] እርሱ ራሱ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ‘ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ’ ይላል።

[37] እንግዲህ፤ እርሱ ራሱ ዳዊት ጌታዬ ያለው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው ያዳምጡት ነበር።

[38] ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው ፥ “ዕወቁ፤ ረጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መመላለስን፥ በገባያም እጅ እንዲነሷቸው ከሚወዱ፥

[39] በምኵuራብም፥ ፊት ለፊት መቀመጥን፥ በማዕድም በላይ መቀመጥን ከሚወዱ ከጸሓፊዎች ተጠበቁ።።

[40] በረዥም ጸሎታቸው እያመካኙ የመበለቶችን ገንዘብ የሚበሉ እነዚህ ጽኑ ፍርድን ይቀበላሉ።”

[41] ጌታችን ኢየሱስም በሙዳየ ምጿት ፊት ለፊት ተቀምጦ፥ በሙዳየ ምጿቱ ገንዘብ የሚጨምሩ ሰዎችን ያይ ነበር፤ ብዙ ባለጸጎችም ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር።

[42] አንዲት ድሃ መበለትም መጥታ ቆንደራጢስ የሚሉትን ሁለት መሐለቅ አገባች።

[43] ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ በሙዳየ ምጿቱ ውስጥ ገንዘብ ካገቡት ሁሉ ይህች ደሃ መበለት አብዝታ አገባች።

[44] ያገቡ ሁሉ ከትርፋቸው አግብተዋልና፤ እርስዋ ግን ከድህነቷ የነበራትን ንብረቷን ሁሉ አግብታለችና።”

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters