Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:17

[1] ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

[2] ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶችን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ሲበሉ አዩአቸው።

[3] ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ስለሚጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ካልታጠቡ እህል አይበሉም ነበር።

[4] ከገበያ የገዙትንም በውኃ ካላጠቡ አይበሉም ነበር፤ ሌላም የሚጠብቁት ብዙ ሥርዐት ነበር፤ ጿውንና ማድጋውን፥ የናስ ዕቃውንና አልጋውንም ያጥቡ ነበር።

[5] ጻፎችና ፈሪሳውያንም ፥ “ደቀ መዛሙርትህ ለምን እንደ ሽማግሎች ወግ አይሄዱም? እጃቸውንስ ሳይታጠቡ ለምን እህል ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት።

[6] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ በእናንተ ላይ መልካም ተናግሮአል፤ እንደ ተጻፈ ‘እነዚህ ሕዝቦች በከንፈራቸው ያከብሩኛል፤ በልባቸው ግን ከእኔ በጣም ይርቃሉ።

[7] የሰው ሥርዐት የሆነ ትምህርትን እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።’

[8] የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ታጠብቃላችሁ፥ ጿን ማድጋንም ማጠብን፥ ሌላውንም ይህን የመሰለውን ሁሉ ታደርጋላችሁ።”

[9] ደግሞ እንዲህ አላቸው ፥ “የራሳችሁን ወግ ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ልታፈርሱ ይገባልን?

[10] ሙሴም አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱና በእናቱ ላይ ክፉ ቃልን የተናገረ ሞትን ይሙት ብሎአችሁ ነበር።

[11] እናንተ ግን ትላላችሁ ፥ ሰው አባቱን ወይም እናቱን ከእኔ የተጠቀምህበት ቐርባን ማለት መባ ነው ቢል፥

[12] ለአባቱ ወይም ለእናቱ ምንም እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም።

[13] ስለ ሠራችሁትም ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ዳግመኛም ይህን የመሰለው የምትሠሩት ብዙ ነው።”

[14] ዳግመኛም ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው ፥ “ሁላችሁም ስሙ፤ አስተውሉም።

[15] ከሰው ልብ የሚወጣው እርሱ ሰውን ያረክሰዋል እንጂ ከውጭ ወደ ሰው አፍ የሚገባው ሊያረክሰው የሚችል አይደለም።

[16] የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”

[17] ከሕዝቡም ተለይቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት።

[18] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ ደግሞ እንዲህ አታስተውሉምን? ከውጭ ወደ ሰው አፍ የሚገባው ሁሉ ሰውን ሊያረክሰው እንደማይችል አታውቁምን?

[19] ወደ ሆዱ ብቻ እንጂ ወደ ልቡ አይገባምና፤ ምግቡንም ሁሉ እያጣራ ወደ ውጭ ያፈስሳል።”

[20] እንዲህም አላቸው ፥ “ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክሰው እርሱ ነው።

[21] ከሰው ልብ ውስጥ ክፉ ዐሳብ ሁሉ ይወጣልና፤ ይኸውም ዝሙት፥ ስርቆት፥ መግደል፥

[22] ማመንዘር፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኮል፥ መዳራት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ምቀኝነት፥ ስንፍና ነው።

[23] ከውስጥ የሚወጣው ይህ ሁሉ ክፉ ነገር ሰውን ያረክሰዋል።”

[24] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ሀገር ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ ማንም ሊያውቀው አልወደደም ነበር፤ ነገር ግን ሊሰወር አልቻለም።

[25] ያንጊዜም ልጅዋን ርኩስ መንፈስ የያዘባት አንዲት ሴት የእርሱን ነገር ሰምታ መጣች፤ ገብታም ከእግሩ በታች ወድቃ ሰገደችለት።

[26] ሴቲቱም አረማዊት ነበረች፤ በትውልዷም ከሶርያና ከፊንቄ ወገን ነበረች፤ ከልጅዋም ጋኔኑን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው።

[27] ጌታችን ኢየሱስ ግን ፥ “ተዪ፤ በመጀመሪያ ልጆች ይጥገቡ፤ የልጆችን እንጀራ ነጥቆ ለውሾች መስጠት መልካም አይደለምና ” አላት።

[28] እርስዋም መልሳ ፥ “አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ውሾችም እኮ ከልጆች የወደቀውን ፍርፋሪ ከገበታ በታች ሆነው ይበላሉ ” አለችው።

[29] እርሱም ፥ “ሂጂ፤ ስለዚህ አነጋገርሽም ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል ” አላት።

[30] ወደ ቤቷም ተመለሰች፤ ልጅዋንም ጋኔኑ ለቆአት፥ ልብስዋንም ለብሳ፥ በአልጋዋም ላይ ተቀምጣ አገኘቻት።

[31] ዳግመኛም ከጢሮስ አልፎ በሲዶና በኩል ዐሥር ከተማ በሚባል ሀገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ።

[32] ዲዳና ደንቆሮ የሆነ ሰውም አምጥተው እጁን እንዲጭንበት ማለዱት።

[33] ብቻውንም ከሰዎች ፈቀቅ አደረገው፤ ጣቶቹንም ወደ ጆሮዎቹ አገባ፤ ምራቁንም እንትፍ ብሎ ምላሱን ዳሰሰው።

[34] ወደ ሰማይም ተመልክቶ አዘነና፤ “ኤፍታህ ” አለ፤ ይህም “ ተከፈት ” ማለት ነው።

[35] ወዲያውኑም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ የምላሱም እስራት ተፈታና አስተካክሎ ተናገረ።

[36] ለማንም እንዳይነግሩ ከለከላቸው፤ ነገር ግን እርሱ የሚከለክላቸውን ያህል እነርሱ ደግሞ ይናገሩለት ነበር።

[37] እጅግም ተደነቁና ፥ “ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ፥ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል ” አሉ።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters