Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:25

[1] የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ ይህ ነው።

[2] በነቢያት እንደ ተጻፈ “እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ።

[3] የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የአዋጅ ነጋሪ ድምፅ፤”

[4] ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኀጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር።

[5] የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር።

[6] የዮሐንስም ልብሱ የግመል ጠጕuር ነበር፤ ወገቡንም በጠፍር መታጠቂያ ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሃ ማር ነበር።

[7] እንዲህም እያለ ይሰብክ ነበር ፥ “ከእኔ ይልቅ የሚበረታ፥ ተጐንብሼ የጫማዉን ማሰሪያ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤

[8] እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።”

[9] ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ፤ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው።

[10] ወዲያውም ከውኃዉ በወጣ ጊዜ፥ ሰማይ ሲከፈት፥ መንፈስ ቅዱስም እንደ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ።

[11] ከሰማይም ፥ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተም ደስ ይለኛል ” የሚል ድምፅ መጣ።

[12] ያንጊዜም መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው።

[13] አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በምድረ በዳ ተቀመጠ፤ ከሰይጣንም ይፈተን ነበር፤ ከአራዊትም ጋር ነበር፤ መላእክትም ያገለግሉት ነበር።

[14] ዮሐንስንም ከያዙት በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ መጥቶ የእግዚአብሔርን የመንግሥት ወንጌል ሰበከ።

[15] እንዲህም አለ ፥ “ጊዜዉ ደረሰ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ።”

[16] በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍም ስምዖንንና ወንድሙ እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አገኛቸው፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና።

[17] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰውንም የምታጠምዱ አደርጋችኋለሁ ” አላቸው።

[18] ያንጊዜም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።

[19] ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጆች ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አገኛቸው፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር ነበር።

[20] ያንጊዜም ጠራቸው፤ አባታቸውን ዘብዴዎስንም ከሙያተኟቹ ጋር በታንኳ ውስጥ ትተው ተከትለውት ሄዱ።

[21] ወደ ቅፍርናሆምም ሄዱ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵuራብ ገብቶ ያስተምራቸው ጀመረ።

[22] ትምህርቱንም አደነቁ፤ እንደ ጻፎቻቸው ያይደለ እንደ በዓለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።

[23] በዚያም ጊዜ በምኵuራባቸው ውስጥ ክፉ ጋኔን ያደረበት ሰው ነበር።

[24] እርሱም ፥ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጥተሃልን? የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ፥ አንተ ማን እንደ ሆንህ ዐውቄሃለሁ ” ብሎ ጮኸ።

[25] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ዝም በልና ከእርሱ ውጣ ” ብሎ ገሠጸው።

[26] ያ ክፉ ጋኔንም አፈራገጠውና በታላቅ ቃል ጮኾ ከእርሱ ወጣ።

[27] ሁሉም አደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም ፥ “ይህ አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን አጋንንትን ውጡ ብሎ ያዝዛቸዋልና፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ” ተባባሉ።

[28] ዝናዉም በገሊላ አውራጃዎች ሁሉ ተሰማ።

[29] ወዲያውም ከምኵuራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ።

[30] የስምዖን አማትም በንዳድ ታማ ነበር፤ ስለ እርስዋም ነገሩት።

[31] ወደ እርስዋም ቀርቦ እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ያንጊዜም ንዳድዋ ተዋት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።

[32] ፀሐይ ገብቶ በመሸ ጊዜም፥ ድውያንንና አጋንንት ያደሩባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ።

[33] የከተማዪቱ ሰዎችም ሁሉ በደጅ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

[34] በልዩ ልዩ ደዌ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሳቸው፤ ብዙዎች አጋንንትንም አወጣ፤ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ዐውቀዋልና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።

[35] በጥዋትም እጅግ ማልዶ ተነሣ፤ ወጥቶም ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ በዚያም ጸለየ።

[36] ስምዖንና አብረውት የነበሩትም ተከተሉት።

[37] ባገኙትም ጊዜ፥ “ሁሉ ይፈልጉሃል ” አሉት።

[38] እርሱም ፥ “ተነሡ፤ ወደ ሌሎች መንደሮችም እንሂድ፤ በዚያ እሰብክ ዘንድ ስለዚህ መጥቻለሁና ” አላቸው።

[39] በገሊላ ሁሉ በየምኵuራባቸው ተዘዋውሮ አስተማረ፤ አጋንንትንም ያወጣ ነበር።

[40] ለምጻም ሰውም ወደ እርሱ መጣ፤ ተንበርክኮም ፥ “አቤቱ፥ ከወደድህስ ልታነጻኝ ትችላለህ ” ብሎ ለመነው።

[41] ጌታችን ኢየሱስም ራራለት፤ እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና ፥ “እፈቅዳለሁ ንጻ ” አለው።

[42] ይህንም በተናገረ ጊዜ ለምጹ ፈጥኖ ለቀቀውና ነጻ።

[43] መክሮም አሰናበተው።

[44] “ለማንም እንዳትናገር ዕወቅ፤ ነገር ግን ሂድና ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ሊሆንባቸው ሙሴ እንዳዘዘ ስለ መንጻትህ መባህን አቅርብ ” አለው።

[45] እርሱ ግን በወጣ ጊዜ እጅግ ይሰብክ ጀመር፤ ዝናዉም ወጣና ተገለጠ፤ በግልጥም ወደ ከተማ መግባት ተሳነው፤ ነገር ግን በምድረ በዳ በውጭ ነበረ፤ ከየስፍራዉም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters