Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:05

[1] ከቤተ መቅደስም በወጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ፥ “መምህር ሆይ፥ ድንጋዩና ሕንጻዉ ምን እንደሚመስል እይ ” አለው።

[2] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ይህን ታላቅ ሕንጻ ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚያ አይቀርም ” አለው።

[3] በቤተ መቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ፥ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻቸው ጠየቁት።

[4] እንዲህም አሉት ፥ “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? ይህ ሁሉስ በሚደረግበት ጊዜ ምልክቱ ምንድን ነው?”

[5] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመረ ፥ “እንዳያስቱአችሁ ተጠንቀቁ።

[6] ብዙዎች ፥ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስቱአቸዋልና።

[7] ጦርነትንና የጦርነትንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ይሆን ዘንድ አለውና፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው።

[8] ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በየቦታዉም የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ረኃብም ይመጣል፤ ይህ የፃዕር መጀመሪያ ነው።

[9] እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ምስክር ሊሆንባቸው ወደ አደባባይ ይወስዱአችኋል፤ በየምኵuራቡም ይገርፉአችኋል፤ ስለ እኔም ወደ አለቆች፥ ወደ ነገሥታትም ያደርሱአችኋል።

[10] ለአሕዛብም ሁሉ አስቀድሞ ወንጌል ሊሰበክ ይገባል።

[11] ወስደውም አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ምን እንደምትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን ያንጊዜ የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ የምትናገሩ አይደላችሁምና።

[12] ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም።

[13] ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ ፍጻሜ የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል።

[14] “ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተነገረውን የጥፋት ርኵuሰት በማይገባው በቅዱስ ቦታ ላይ ቆሞ በአያችሁ ጊዜ የሚያነብበው ያስተውል፤ ያንጊዜም በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።

[15] በሰገነት ላይ ያለም ወደ ምድር ቤት አይውረድ፤ በቤቱ ውስጥ ያለውንም ይወስድ ዘንድ አይግባ።

[16] በዱር ያለም ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላዉ አይመለስ።

[17] ነገር ግን በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።

[18] ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ።

[19] በዚያ ወራት እግዚአብሔር ዓለሙን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ እንደ እርሱ ያልሆነ፥ እንግዲህም ደግሞ የማይሆን ጽኑ መከራ ይሆናልና።

[20] እግዚአብሔር እነዚያን ቀኖች ባያሳጥራቸው ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን፥ እግዚአብሔር ስለ መረጣቸው ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።

[21] ያንጊዜ ‘ክርስቶስ በዚህ አለ፤ ወይም በዚያ ነው ’ የሚላችሁ ቢኖር አትመኑ።

[22] ሐሰተኟች መሢሖችና ሐሰተኟች ነቢያት ይመጣሉና፤ ለማሳትም ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ያደርጋሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትንም ባሳቱአቸው ነበር።

[23] እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ ሁሉን አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።

[24] “ነገር ግን ያንጊዜ ከዚህ ሁሉ መከራ ጋር ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።

[25] ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኀይላት ይናወጣሉ።

[26] ያንጊዜም የሰውን ልጅ በብዙ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።

[27] ያንጊዜም መላእክትን ይልካቸዋል፤ የተመረጡትንም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ከአራቱ ማዕዘን ይሰበስቡአቸዋል።

[28] ምሳሌውንም ከበለስ ዕወቁ፤ ጫፍዋ የለመለመ፥ ቅጠልዋም ያቈጠቈጠ እንደ ሆነ ያንጊዜ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ።

[29] እንዲሁ እናንተም ይህን ሁሉ እንደ ሆነ ባያችሁ ጊዜ፤ ከደጃፍ እንደ ደረሰ ዕወቁ።

[30] እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ ሳይደረግ ይህቺ ትውልድ አታልፍም።

[31] ሰማይና ምድር ያልፋል፥ ቃሌ ግን አያልፍም።

[32] “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም።

[33] ጊዜዉ መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፥ ጸልዩም።

[34] ቤቱን ትቶ ለአገልጋዮቹም ከእነርሱ ለእያንዳንዳቸው ሥራቸውን ሰጥቶ በረኛውንም እንዲተጋ አዝዞ ወደ ሩቅ ሀገር እንደሚሄድ ሰው ነውና።

[35] እንግዲህ ባለቤቱ መቼ እንደሚመጣ፥ በማታ፥ ወይም በመንፈቀ ሌሊት፥ ወይም ዶሮ ሲጮኽ፥ ወይም በማለዳ እንደ ሆነ አታውቁምና፥

[36] ድንገት እንዳይመጣባችሁ፥ ተኝታችሁም እንዳያገኛችሁ፥ ትጉ፤

[37] እነሆ፥ ለእናንተ የምናገረውን ለሁሉ እላለሁ ትጉ።”

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters