[1] ከዚያም ወጥቶ ወደ ሀገሩ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
[2] በሰንበትም በምኵuራብ ያስተምር ጀመረ፤ ብዙዎችም ያዳምጡት ነበር፤ “ይህ ሁሉ ነገር ለእርሱ ከየት ተሰጠው? የተሰጠችው ይህች ጥበብስ ምንድን ናት? በእጁም የሚደረገው ይህ ኀይል ምንድን ነው?” እያሉ ያደንቁ ነበር።
[3] “ይህ ጸራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ፥ ይሁዳና ስምዖንስ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደለምን?” እያሉ ይሰናከሉበት ነበር።
[4] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “በሀገሩ፥ በወገኑና በዘመዶቹ ካልሆነ በቀር ነቢይ አይናቅም።”
[5] እጁን ጭኖ ካዳናቸው ከጥቂት ድውያንም በቀር በዚያ ተአምራትን አላደረገም።
[6] ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ፤ በመንደሮችም እያስተማረ ይመላለስ ነበር።
[7] ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስት ላይም ሥልጣን ሰጣቸው።
[8] ለመንገድም ከበትር ብቻ በቀር እንጀራም ቢሆን፥ከረጢትም ቢሆን፥ መሐለቅም በመታጠቂያቸው እንዳይዙ አዘዛቸው።
[9] በእግራቸው ካለው ጫማ በቀርም ሁለት ልብስ እንዳይለብሱ አዘዛቸው።
[10] እንዲህም አላቸው ፥ “ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በገባችሁበት ቤት በዚያው ተቀመጡ።
[11] ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ሀገርም ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ሊሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ በፍርድ ቀን ሰዶምና ገሞራ ዕረፍትን ያገኛሉ።”
[12] ወጥተውም ሁሉ ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ።
[13] ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውያንንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
[14] ንጉሥ ሄሮድስም ሰማ፤ “ስሙ ግልጥ ሆኖአልና፥ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኀይል ይረዳዋል ” አለ።
[15] “ኤልያስ ነው ያሉም ነበሩ፥ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው ” ያሉም ነበሩ፤
[16] ሄሮድስ ግን ሰምቶ ፥ “ይህ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል ” አለ።
[17] ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ጭፍሮቹን ልኮ ዮሐንስን ይዞ አስሮት ነበር፤
[18] ዮሐንስ ሄሮድስን ፥ “የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ” ይለው ነበርና።
[19] ሄሮድያዳም ጠልታው ነበርና ልታስገድለው ትሻ ነበር፤ ነገር ግን አልተቻላትም።
[20] ሄሮድስም ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና ዮሐንስን ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ በእርሱም ዘንድ ብዙ ይሰማ ነበር፤ ደስ እያለውም ይሰማው ነበር።
[21] ሄሮድስም የተወለደባትን ቀን በዓል በአደረገ ጊዜ መኳንንቱንና የሻለቆቹን፤ የገሊላንም ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።
[22] የሄሮድያዳ ልጅም ምቹ ጊዜ ሆነላትና ገብታ ዘፈነች፤ ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር በማዕድ የተቀመጡትንም ደስ አሰኘቻቸው፤ ንጉሡም ብላቴናይቱን ፥ “የምትሺውን ለምኝኝ፥ እሰጥሻለሁ ” አላት።
[23] እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስ ቢሆንም እንኳ የለመነችውን ሁሉ ሊሰጣት ማለላት።
[24] ወጥታም እናቷን ፥ “ምን ልለምነው?” አለቻት፤ እርስዋም ፥ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ ” አለቻት።
[25] ያንጊዜም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ ” ብላ ለመነችው።
[26] ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ ስለ መሐላው፥ ከእርሱም ጋር በማዕድ ስለ ተቀመጡት ሰዎች እንቢ ሊላት አልወደደም።
[27] ያንጊዜም ንጉሡ ከጭፍሮቹ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘ። ሄዶም የዮሐንስን ራስ በግዞት ቤት ቈረጠ፤
[28] ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለዚያች ብላቴና ሰጣት፤ ብላቴናይቱም ለእናቷ ሰጠች።
[29] ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ፤ ሄዱና የዮሐንስን በድን ወስደው ቀበሩት።
[30] ሐዋርያትም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት።
[31] “ኑ ለብቻችን ወደ ምድረ በዳ እንውጣና ጥቂት ዕረፉ ” አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፤ እህልም ይበሉ ዘንድ እንኳ ጊዜ አላገኙም።
[32] ብቻቸውንም በታንኳ ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።
[33] ብዙዎቹም ሲሄዱ አይተው ዐወቁአቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸው፤ ወደ እርሱም መጡ።
[34] ጌታችን ኢየሱስም በወጣ ጊዜ፥ ብዙ ሰዎችን አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፤ ብዙም ያስተምራቸው ጀመረ። ማቴ.
[35] ከብዙ ሰዓት በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት ፥ “ይህ ስፍራ ምድረ በዳ ነው፤ ጊዜውም ፈጽሞ መሽቶአል።
[36] የሚበሉትም የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብት።”
[37] እርሱም መልሶ ፥ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው ” አላቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ይበሉ ዘንድ እንድንሰጣቸው በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ለመግዛት እንሂድን?” አሉት።
[38] “ሂዱና ስንት እንጀራ እንዳላችሁ እዩ ” አላቸው፤ አይተውም ፥ “አምስት እንጀራ ሁለትም ዓሣ አለን ” አሉት።
[39] ሁሉንም በለመለመ መስክ ላይ በየክፍሉ እንዲያስቀምጧቸው አዘዛቸው።
[40] መቶ መቶውና አምሳ አምሳው ሆነው በተራ ተቀመጡ።
[41] አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አየ፤ እንጀራውንም ባረከ፤ ቆርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ሁለቱንም ዓሣዎች ለሁሉ ከፈለ።
[42] ሁሉም በልተው ጠገቡ።
[43] ከቐርስራሹም፥ ከዓሣውም ደግሞ ዐሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ።
[44] እንጀራውንም የበሉት ወንዶች አምስት ሺህ ነበሩ።
[45] ያንጊዜም እርሱ ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ወደ ታንኳው ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ ይቀድሙት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን ግድ አላቸው።
[46] እነርሱንም አሰናብቶ ከዚያ ሄደ፤ ሊጸልይም ወደ ተራራ ወጣ።
[47] በመሸም ጊዜ ታንኳዪቱ በባሕር መካከል ነበረች፤ እርሱ ግን ብቻውን በየብስ ላይ ነበረ።
[48] ነፋስ ከፊታቸው ነበርና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አያቸው፤ በአራተኛው ክፍለ ሌሊትም ጌታችን ኢየሱስ ባሕሩን እየረገጠ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድድ ነበር።
[49] በባሕር ላይ ሲሄድም ባዩት ጊዜ ምትሀት መስሏቸው ጮኹ።
[50] ሁሉም አዩትና ደነገጡ፤ ያንጊዜም ተናገራቸውና “አይዞአችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ ” አላቸው።
[51] ወደ እነርሱም ወደ ታንኳው ውስጥ ገባ፤ ነፋሱም ፀጥ አለ፤ እጅግም ተገረሙ።
[52] ልባቸውም ደንዝዞ ነበርና ስለ እንጀራው አላስተዋሉም ነበር።
[53] ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ፤ ታንኳቸውንም በዚያ አስጠጉ።
[54] ከታንኳው ሲወጡም ወዲያውኑ የዚያች ሀገር ሰዎች ዐወቁት።
[55] በየመንደሩም ሁሉ ሮጡ፤ በሽተኟችንም በአልጋ አመጡ፤ እርሱም በዚያ እንዳለ ወደ ሰሙበት ቦታ ወሰዱ።
[56] በገባበትም ቦታ ሁሉ በየከተማው፥ በየመንደሩና በየገጠሩ በሽተኟችን በገበያዎች ያስቀምጡ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንዲዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ይድኑ ነበር።