[1] በነጋ ጊዜም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሓፊዎች ሸንጎውም ሁሉ ተማከሩ፤ ጌታችን ኢየሱስንም አስረው ወስደው ለጲላጦስ ሰጡት።
[2] ጲላጦስም ፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተ ትላለህ ” አለው።
[3] የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት፤ እርሱ ግን የመለሰው ነገር የለም።
[4] ጲላጦስም ፥ “ይህን ያህል ሲከስሱህ አንዳች አትመልስምን?” ብሎ እንደገና ጠየቀው።
[5] ጌታችን ኢየሱስ ግን ጲላጦስ እስኪያደንቀው ድረስ ምንም አልመለሰለትም።
[6] በየበዓሉም ከእስረኟች የመረጡትን አንዱን ይፈታላቸው ነበር።
[7] ከክፉ አድራጊዎችና ከነፍሰ ገዳዮች ጋር የታሰረ ስሙ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበር።
[8] ሕዝቡም ወጥተው እንደ አስለመደ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ለመኑ።
[9] ጲላጦስም መልሶ ፥ “የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን?” አላቸው።
[10] የካህናት አለቆች በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።
[11] የካህናት አለቆች ግን በርባንን እንዲፈታላቸው ይለምኑት ዘንድ ሕዝቡን አነሣሡአቸው።
[12] ጲላጦስም መልሶ ፥ “እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ?” አላቸው።
[13] እነርሱም እንደገና ፥ “ስቀለው ” እያሉ ጮኹ።
[14] ጲላጦስም ፥ “ምን ክፉ ሥራ ሠራ?” አላቸው፤ እነርሱ ግን ፥ “ስቀለው ” እያሉ አብዝተው ጮኹ።
[15] ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወድዶ በርባንን ፈታላቸው፤ ጌታችን ኢየሱስንም ገርፎ ሊሰቅሉት ሰጣቸው።
[16] ወታደሮችም ወደ ግቢ ውስጥ ወደ ፍርድ ሸንጎ አገቡት፤ ባለወጎቹንም ጭፍሮች ሁሉ ጠሩ።
[17] ቀይ ሐርም አለበሱት፤ የእሾህ አክሊልም ጐንጕuነው ደፉበት፤ ተዘባበቱበትም።
[18] “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ” አሉት።
[19] ራሱንም በዘንግ ይመቱትና ይተፉበት፥ ተንበርክከውም በፊቱ ይሰግዱለት ነበር።
[20] ከተዘባበቱበትም በኋላ ያን ቀይ ሐር ገፈፉት፤ ልብሱንም አልብሰው ወደሚሰቅሉበት ቦታ ወሰዱት።
[21] ስምዖን ቀሬናዊ የተባለ አንድ መንገድ አላፊ እርሱም የእስክንድሮስና የሩፎስ አባት ከዱር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።
[22] በትርጓሜው የራስ ቅል ወደሚሉት ቦታ ጎልጎታ ወደሚባል ስፍራ ወሰዱት።
[23] ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ ወይን እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም አለ።
[24] ሰቀሉትም፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጥለው እንደ ድርሻቸው ተካፈሉ።
[25] ሲሰቅሉትም ሦስት ሰዓት ነበር።
[26] የበደሉ ደብዳቤም “የአይሁድ ንጉሥ ነው ” ይል ነበር።
[27] ከእርሱ ጋርም ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራዉ ሰቀሉ።
[28] መጽሐፍም ፥ “ከዐመፀኟች ጋር ተቈጠረ ” ያለው ተፈጸመ።
[29] መንገድ ተላላፊዎችም ይሰድቡት ነበር፤ ራሳቸውንም እየነቀነቁ እንዲህ ይሉት ነበር ፥ “ቤተ መቅደስን የምታፈርሰው፥ በሦስት ቀንም የምትሠራው ሆይ፥
[30] ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን፤”
[31] እንዲሁ የካህናት አለቆችና ጸሓፊዎችም እየዘበቱበት “ሌላውን የሚያድን፥ ራሱን ማዳን የማይችል ” ይሉት ነበር።
[32] “እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ ከሆነ እስኪ አሁን ከመስቀሉ ይውረድና አይተን እንመንበት፤” አሉ፤ አብረውት የተሰቀሉትም ያሽሙአጥጡት ነበር።
[33] ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ ምድርም ሁሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ።
[34] ዘጠኝ ሰዓትም በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በታላቅ ቃል ፥ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።
[35] በዚያ ቆመው ከነበሩትም ፥ “ኤልያስን ይጠራል ” አሉ።
[36] አንዱም ሮጠና ሰፍነጉን መጻጻ መልቶ በዘንግ አስሮ አጠጣውና ፥ “ዝም በሉ፤ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ ” አለ።
[37] ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱንም ከሥጋው ለየ።
[38] የቤተ መቅደሱ መጋረጃም ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።
[39] ፊት ለፊት የቆመው የመቶ አለቃም እንዲህ ጮኾ እንደ ሞተ ባየ ጊዜ ፥ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው ” አለ።
[40] ከሩቅም ቆመው የሚያዩት ሴቶች ነበሩ፤ እነርሱም ማርያም መግደላዊት፥ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም ነበሩ።
[41] እነዚህም ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ሌሎችም ብዙዎች ከእርሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ነበሩ።
[42] ያንጊዜም ዐርብ ሲመሽ የሰንበት መግቢያ ነበር።
[43] ደግና ምክር ዐዋቂ የነበረ ሰው፥ እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት ተስፋ ያደርግ የነበረ የአርማትያሱ ዮሴፍ መጣ፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ለመነ።
[44] ጲላጦስም ፥ እንዴት እንደ ሞተ አደነቀ፤ ወታደሩንም ጠርቶ ፥ “ፈጽሞ ሞተን?” አለው፤ ወታደሩም ፥ “አዎን፥ ሞተ ” አለው።
[45] እንደ ሞተም ከወታደሩ ተረድቶ ሥጋዉን ለዮሴፍ እንዲሰጡት አዘዘ።
[46] ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ አውርዶም በበፍታ ገንዞ ከዐለት ባስፈለፈለው አዲስ መቃብር ቀበረው፤ ድንጋይም አገላብጦ የመቃብሩን አፍ ገጠመ።
[47] ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያምም የቀበሩበትን አዩ።