Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:05

[1] ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ፤

[2] ከታንኳውም በወረደ ጊዜ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ወጥቶ ተገናኘው።

[3] እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፤ ማንም በእግር ብረት እንኳ ቢሆን ያሥረው ዘንድ አይችልም ነበር።

[4] ዘወትር በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና፥ ነገር ግን እግር ብረቱን ይሰብርና ሰንሰለቱን ይቀጠቅጥ ነበር፤ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም።

[5] ዘወትርም በመቃብርና በተራራ፥ በመዐልትና በሌሊት ይጮህ ነበር፤ ሰውነቱንም በባልጩት ይቈርጥ ነበር።

[6] ጌታችን ኢየሱስንም ከሩቅ ባየው ጊዜ ሮጦ ሰገደለት።

[7] በታላቅ ድምፅም እየጮኸ ፥ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ ” አለው።

[8] ያን ርኩስ መንፈስ ከእርሱ ውጣ ብሎት ነበርና።

[9] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ስምህ ማነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ፥ “ስሜ ሌጌዎን ነው፤ እኛ ብዙዎች ነንና ” አለው።

[10] ከሀገርም አስወጥቶ እንዳይሰድደው አብዝቶ ማለደው።

[11] ከዚያም በተራራው አጠገብ ብዙ የዕሪያ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።

[12] እነዚያ አጋንንትም ፥ “እናድርባቸው ዘንድ ወደ ዕሪያዎች ስደደን ” ብለው በብዙ ማለዱት።

[13] ጌታችን ኢየሱስም ፈቀደላቸው፤ እነዚያ ርኩሳን መናፍስትም ወጥተው ወደ ዕሪያዎች ገቡ፤ መንጋዎቹም በርግገው ወደ ባሕሩ ተወረወሩ፤ እነርሱም ሁለት ሺህ ያህል ነበሩ፤ በባሕሩ ውስጥም ሰጠሙ።

[14] እረኟችም ሸሽተው በከተሞችና በመንደሮች ተናገሩ፤ እነርሱም የሆነውን ሊያዩ መጡ።

[15] ወደ ጌታችን ኢየሱስም መጡ፤ ጋኔን የያዘውን፥ ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ልቡ ተመልሶለት፥ ልብሱንም ለብሶ ተቀምጦ አዩትና ፈሩ።

[16] ያዩ ሰዎችም ጋኔን ለያዘው ሰው የሆነውንና በዕሪያዎቹም የተደረገውን ነገሩአቸው።

[17] ከሀገራቸውም ይወጣ ዘንድ ይማልዱት ጀመሩ።

[18] ወደ ታንኳው በወጣ ጊዜም ያ ጋኔን የወጣለት ሰው ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ማለደው።

[19] ጌታችን ኢየሱስም ከለከለው፤ “ወደ ቤትህ ወደ ወገኖችህ ሂድ፤ እግዚአብሔር ያደረገልህንም ታላቅ ነገር ሁሉ፤ ይቅር እንዳለህም ተናገር ” አለው።

[20] ሄዶም ጌታችን ኢየሱስ ያደረገለትን ሁሉ በዐሥሩ ከተሞች ይሰብክ ጀመር፤ ሁሉም አደነቁ።

[21] ዳግመኛም፥ ጌታችን ኢየሱስ በታንኳው ወደ ማዶ ተሻገረ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በባሕር ዳርም ነበረ።

[22] እነሆ ስሙ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵuራብ ሹም የነበረ አንድ ሰው ወደ እርሱ መጣና አገኘው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት።

[23] “ልጄ ልትሞት ደርሳለች፤ ነገር ግን ና እጅህን ጫንባት፤ ትድናለችም ” እያለ አብዝቶ ማለደው።

[24] ጌታችን ኢየሱስም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ይጋፉትም ነበር።

[25] ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈስሳት የነበረች ሴት ነበረች።

[26] ከብዙዎች ባለ መድኀኒቶችም እጅግ ደከመች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ሰጥታ ጨረሰች፤ ነገር ግን እጅግ ባሰባት እንጂ ምንም የጠቀማት የለም።

[27] የጌታችን ኢየሱስን ነገር በሰማች ጊዜ መጣችና በሰው መኃል ገብታ በስተኋላው የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች።

[28] የልብሱን ጫፍ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና።

[29] ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ፤ ከደዌዋም እንደ ዳነች ራስዋ ዐወቀች።

[30] ጌታችን ኢየሱስም ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፥ ወደ ሰዎች መለስ ብሎ ፥ “ልብሴን ማን ዳሰሰ?” አላቸው።

[31] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ሕዝቡ ሲጋፋህ ታያለህ፤ አንተ ግን ማን ዳሰሰኝ? ትላለህ ” አሉት።

[32] ይህንም ያደረገውን ያይ ዘንድ ዘወር አለ።

[33] ሴቲቱም የተደረገላትን ስላወቀች ፈራች፤ እጅግም ተንቀጠቀጠች፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም መጥታ ሰገደችለት፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው

[34] እርሱም ፥ “ልጄ ሆይ፥ ሃይማኖትሽ አዳነችሽ፥ በሰላም ሂጂ፤ ከደዌሽ ተፈወሺ ” አላት።

[35] ከእርስዋ ጋር ሲነጋገርም ሰዎች ከምኵuራቡ ሹም ቤት መጥተው ፥ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህርን አታድክመው ” አሉት።

[36] ጌታችን ኢየሱስም ሲያነጋግሩት በሰማ ጊዜ፥ የምኵuራቡን ሹም ፥ “እመን እንጂ አትፍራ ” አለው።

[37] ከጴጥሮስና ከያዕቆብ፥ ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስም በቀር የሚከተለው ማንም እንዳይኖር ከለከለ።

[38] ወደ ምኵuራቡ ሹም ቤት በገባ ጊዜም ሲታወኩና፥ ሲያለቅሱ፥ እጅግም ሲጮኹ አገኛቸው።

[39] ገብቶም ፥ “ለምን ትጮኃላችሁ? ለምንስ ታለቅሳላችሁ? ልጅቱስ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም ” አላቸው።

[40] በጣምም ሳቁበት፤ እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናት፥ ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞአቸው ብላቴናይቱ ወደ አለችበት ገባ።

[41] የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ ፥ “ጣሊታ ቁሚ ” አላት፤ ትርጓሜውም “አንች ብላቴና ተነሺ ” ማለት ነው።

[42] ያንጊዜም ያቺ ብላቴና ተነሥታ ወዲያና ወዲህ አለች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ ያንጊዜም ታላቅ መደነቅን ተደነቁ።

[43] ይህንም የሚያውቅ ማንም እንዳይኖር በብዙ መከራቸው፤ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters