Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 10:51

[1] ከሁለት ቀንም በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ፤ የካህናት አለቆችና ጸሓፊዎችም ሊተናኰሉት፥ ሊይዙትና ሊገድሉት ይሹ ነበር።

[2] ሕዝቡም እንዳይታወኩ “በበዓል አይሁን ” አሉ።

[3] እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በማዕድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋዉ የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡንም ከፍታ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

[4] እንዲህም ብለው የተቈጡ ነበሩ ፥ “የዚህ ሽቱ ጥፋት ይህን ያህል ለምንድን ነው?

[5] ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ለነዳያን ሊሰጥ ባልተቻለም ነበር?” እርስዋንም ገሠጹአት።

[6] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “ሴቲቱን ተዉአት፤ አታድክሙአትም፤ ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታለች።

[7] ነዳያንንስ ዘወትር በእናንተ ዘንድ ታገኙአቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ መልካም ታደርጉላቸዋላችሁ፤ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም።

[8] ይህቺም ያላትን አደረገች፤ አስቀድማም ለቀብሬ ሥጋዬን ቀባች።

[9] እውነት እላችኋለሁ፤ ይህን ወንጌል በሚሰብኩበት በዓለሙ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውን ይናገሩላታል፤ ያስቡአታልም።”

[10] ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ያስቆሮቱ ሰው ይሁዳም ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።

[11] ሰምተውም ደስ አላቸውና ሠላሳ ብር ሊሰጡት ተዋዋሉት፤ በስውርም አሳልፎ ሊሰጣቸው ይሻ ነበር።

[12] የፋሲካዉንም በግ በሚያርዱበት በመጀመሪያው የቂጣ በዓል ቀን ደቀ መዛሙርቱ ፥ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ፥ ወዴት ሄደን ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት።

[13] ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “በፊታችሁ ወደ አለችው ከተማ ሂዱ፤ የውኃ ማድጋ የተሸከመ ሰውም ታገኛላችሁ፤ እርሱንም ተከተሉት።

[14] ወደ ገባበትም ቤት ገብታችሁ፥ ባለቤቱን ፥ መምህር ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ፋሲካን የምበላበት አዳራሽ ወዴት ነው? ብሎሃል በሉት።

[15] እርሱም የተነጠፈና የተዘጋጀ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።”

[16] ደቀ መዛሙርቱም ወደ ከተማ ሄዱ፤ እንዳላቸውም አገኙና ፋሲካን አዘጋጁ።

[17] በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሄደ።

[18] በማዕድም ላይ ተቀምጠው ሲበሉ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው ያሲዘኛል።”

[19] እያንዳንዳቸውም ፥ “ከቶ እኔ እሆን?” እያሉ ይተክዙ ጀመር።

[20] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ ከእኔ ጋር እጁን ወደ ወጭቱ የሚያጠልቀው ነው።

[21] የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን፥ የሰው ልጅ በእጁ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ በተሻለው ነበር።”

[22] ሲበሉም ጌታችን ኢየሱስ ኅብስቱን አንሥቶ ባርኮ ቈርሶም ፥ “ይህ ሥጋዬ ነው፤ እንኩ ብሉ ” ብሎ ሰጣቸው።

[23] ጿዉንም አንሥቶ አመስግኖ ፥ “እንኩ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ ” ብሎ ሰጣቸው።

[24] እንዲህም አላቸው ፥ “ስለ ብዙዎች የሚፈስሰው የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።

[25] እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲስ አድርጌ እስከምጠጣባት እስከዚያች ቀን ድረስ እንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ አልጠጣም።”

[26] የምስጋና መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

[27] ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው ፥ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ ‘ጠባቂዉን እገድለዋለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ ’ የሚል ጽሑፍ አለና።

[28] ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ።”

[29] ጴጥሮስም ፥ “ሁሉም ቢክዱህ እንኳን እኔ ከቶ አልክድህም ” አለው።

[30] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” አለው።

[31] ጴጥሮስ ግን ቃሉን አበርትቶ ፥ “ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም ” አለ። ሁሉም እንደ እርሱ አሉ።

[32] ጌቴሴማኒ ተብላ ወደምትጠራ የአትክልት ቦታም ሄዱ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ፥ “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ ድረስ በዚህ ተቀመጡ ” አላቸው።

[33] ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰዳቸው፤ ያዝንና ይተክዝም ጀመረ።

[34] እንዲህም አላቸው ፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ተቀመጡ፤ እንግዲህም ትጉ።”

[35] ከዚህም በኋላ፥ ጥቂት እልፍ ብሎ በምድር ላይ ሰገደ፤ ይቻል እንደሆነም ያቺ ሰዓት ከእርሱ ታልፍ ዘንድ ጸለየ።

[36] “አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህቺን ጿ ከእኔ አሳልፋት፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን፤ የእኔ ፈቃድም አይደለም።”

[37] በተመለሰ ጊዜም ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው ፥ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አትችልምን?

[38] ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ይሻልና፥ ሥጋ ግን ይደክማልና።”

[39] ዳግመኛም ሄዶ ጸለየ፤ ያንኑ ቃል ብቻም ተናገረ።

[40] ዳግመኛም በተመለሰ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው ነበርና፤ የሚናገሩትንም አያውቁም ነበርና።

[41] በሦስተኛውም መጥቶ እንዲህ አላቸው ፥ “እንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ አሁን ጊዜዉ ደርሶአልና፤ እነሆ፥ የሰውን ልጅ በኃጥኣን እጅ አሳልፈው ይሰጡታል።

[42] ተነሡ እንሂድ፤ እነሆ፥ የሚያሲዘኝ መጥቶአል።”

[43] ሲነጋገራቸውም ወዲያውኑ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ያስቆሮቱ ሰው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ከካህናት አለቆች፥ ከጸሓፊዎችና ከሽማግሎችም የተላኩ፥ ሾተልና ጎመድ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ።

[44] የሚያሲዘውም ምልክት ሰጣቸው ፥ “የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ” አላቸው።

[45] ያንጊዜም ወደእርሱ መጣና ፥ “መምህር ሆይ፥” ብሎ ሳመው።

[46] በእርሱም ላይ እጃቸውን ዘርግተው ያዙት።

[47] ከእርሱ ጋር ቆመው ከነበሩትም አንዱ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ጆሮውንም ቈረጠው።

[48] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እንደ ሌባ ተከታትላችሁ በሾተልና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን?

[49] በመቅደስም ሳስተምር ዘወትር ከእናንተ ጋር ስኖር፥ አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን በመጻሕፍት ያለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።”

[50] ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ።

[51] ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጐልማሳም ይከተለው ነበር፤ ጐልማሶችም ያዙት።

[52] እርሱ ግን ነጠላዉን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።

[53] ጌታችን ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆች፥ ጸሓፊዎችና ሽማግሎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

[54] ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ድረስ ከሩቁ ተከተለው፤ በብርሃኑ በኩልም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር።

[55] የካህናት አለቆችና ሸንጎዎች ሁሉ ይገድሉት ዘንድ ጌታችን ኢየሱስን ይከስሱት ዘንድ የሐሰት ምስክሮችን ፈለጉ፤ ነገር ግን አጡ።

[56] በሐሰትም የመሰከሩበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ቃላቸው አንድ አልሆነም።

[57] ተነሥተውም በሐሰት የተናገሩ የሐሰት ምስክሮች ነበሩ።

[58] “እኔ ይህን የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስተኛው ቀን የሰው እጅ ያልሠራው ሌላ ቤተ መቅደስ እሠራለሁ ሲል እኛ ሰምተነዋል ” አሉ።

[59] ከዚህም ጋር ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም።

[60] ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ ፥ “እነዚህ ይህን ያህል ሲመሰክሩብህ የምትመልሰው አንዳች የለህምን?” ብሎ ጌታችን ኢየሱስን ጠየቀው።

[61] እርሱ ግን ዝም አለ፥ ምንም አልመለሰለትም፤ ሊቀ ካህናቱም ዳግመኛ መረመረው፤ “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” አለው።

[62] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አዎን፥ እኔ ነኝ፤ የሰውን ልጅ በኀይል ቀኝ ተቀምጦ፤ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ ” አለው።

[63] ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀድዶ እንዲህ አለ ፥ “እንግዲህ ምን ምስክር ትሹለታላችሁ?

[64] እነሆ፥ እናንተ ራሳችሁ ስድቡን ሰማችሁ፤ እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” ሁሉም ፥ “ሞት ይገባዋል ” ብለው ፈረዱበት።

[65] ከመካከላቸውም አንዳንዶች ይተፉበት ነበር፤ ፊቱንም ሸፍነው ራሱን ይመቱትና፤ “ክርስቶስ፥ ትንቢት ተናገር ” ይሉት ነበር፤ ሎሌዎችም መላልሰው በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

[66] ጴጥሮስም በግቢው ውስጥ በታች ቤት ሳለ፥ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲት ብላቴና መጣች።

[67] ጴጥሮስንም እሳት ሲሞቅ አየችው፤ አስተውላም ፥ “አንተ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ ” አለችው።

[68] እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም፤ ልብም አላደርገውም ” ብሎ ካደ፤ ከቅፅሩም ወደ ውጭ ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ።

[69] ዳግመኛም ሌላዪቱ ብላቴና አየችውና ከዚያ ቆመው ለነበሩት ፥ “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ” አለቻቸው፤ እርሱም ሁለተኛ ካደ።

[70] ከጥቂት ጊዜም በኋላ ከዚያ ቆመው የነበሩት ጴጥሮስን ፥ “በእውነት አንተ ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አንተ ገሊላዊ ነህና፤ አነጋገርህም ያስታውቅብሃል ” አሉት።

[71] እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ” እያለ ይምልና ይረገም ጀመር፤ ያንጊዜም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ።

[72] ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” ያለውን፤ የጌታችን የኢየሱስን ቃል ዐስቦ አለቀሰ።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters