[1] ከዚያም ሲያልፍ ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ።
[2] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኀጢኣት ነው? በራሱ ነውን? ወይስ በወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት።
[3] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፤ ወላጆቹም አልበደሉም።
[4] ነገር ግን ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ልሠራ ይገባኛል፤ ማንም ሥራ ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና።
[5] በዓለም ሳለሁ፤ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”
[6] ይህንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዕዉሩን ዐይኖች ቀባው።
[7] እንዲህም አለው ፥ “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ ” ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው፤ ሄዶም ታጠበና እያየ ተመለሰ።
[8] ጎረቤቶቹና ቀድሞ የሚያውቁት፥ ሲለምንም ያዩት የነበሩት ግን ፥ “ይህ በመንገድ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም?” አሉ።
[9] “ይህ እርሱ ነው ” ያሉ አሉ፤ ሌሎችም ፥ “አይደለም፤ ይመስለዋል እንጂ ” አሉ፤ እርሱ ራሱ ግን ፥ “እኔ ነኝ ” አለ።
[10] እነርሱም ፥ “ዐይኖችህ እንዴት ተገለጡ?” አሉት።
[11] እርሱም መልሶ ፥ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው በምራቁ ጭቃ አድርጎ ዐይኖቼን ቀባኝና ሂደህ በሰሊሆም ውኃ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄም ታጠብሁና አየሁ ” አላቸው።
[12] አይሁድም ፥ “ሰውየው የት አለ?” አሉት፤ እርሱም ፥ “አላውቅም ” አላቸው።
[13] ያን ዕዉር ሆኖ የተወለደውንም ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት።
[14] ጌታችን ኢየሱስ በምራቁ ጭቃ አድርጎ ዐይኖቹን ያበራበት ቀኑ ሰንበት ነበርና።
[15] ፈሪሳውያንም እንዴት እንዳየ ዳግመኛ ጠየቁት፤ እርሱም ፥ “በምራቁ ጭቃ አድርጎ በዐይኖቼ አኖረው፥ ታጥቤም አየሁ ” አላቸው።
[16] ከፈሪሳውያንም አንዳንዶች ፥ “ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ሰንበትን አያከብርምና ” አሉ፤ ሌሎች ግን “ኀጢኣተኛ ሰው እንዲህ ያለ ተአምራት ማድረግ እንዴት ይችላል?” አሉ፤ እርስ በርሳቸውም ተለያዩ።
[17] ዳግመኛም ዕዉሩን ፥ “አንተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ዐይኖችህን ከፍቶልሃልና ” አሉት፤ እርሱም ፥ “ነቢይ ነው ” አላቸው።
[18] አይሁድም የዚያን ያየውን ሰው ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕዉር ሆኖ እንደ ተወለደ፥ እንዳየም አላመኑም።
[19] “ዕዉር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? እንግዲያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው።
[20] ወላጆቹም መልሰው እንዲህ አሉ ፥ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነ፥ ዕዉር ሆኖም እንደ ተወለደ እናውቃለን።
[21] አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ ዐይኖቹንም ማን እንደ አበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ ዐዋቂ ነውና፤ ስለ ራሱም መናገር ይችላልና።”
[22] ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ ፥ “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር ከምኵuራብ ይውጣ ” ብለው አይሁድ ተስማምተው ነበርና።
[23] ስለዚህም ወላጆቹ ፥ “ዐዋቂ ነውና እርሱን ጠይቁት ” አሉ።
[24] ዕውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው ፥ “ሂድ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርብ፤ ይህ ሰው ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን ” አሉት።
[25] ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እርሱ ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኔ አላውቅም፤ እኔ ዕዉር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ብቻ አውቃለሁ።”
[26] ዳግመኛም ፥ “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ እንደምን አበራልህ?” አሉት።
[27] እርሱም መልሶ ፥ “አትሰሙኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እንግዲህ ደግሞ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?” አላቸው።
[28] እነርሱም ሰደቡት፤ እንዲህም አሉት ፥ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሁን፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን።
[29] እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተነጋገረው እናውቃለን፤ ይህን ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም።”
[30] ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ከወዴት እንደ ሆነ፥ አታውቁትምና ይህ እጅግ ድንቅ ነው፤ ነገር ግን ዐይኖቼን አበራልኝ።
[31] እኛም እግዚአብሔርን የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እርሱን ይሰማዋል እንጂ ኃጥኣንን እንደማይሰማቸው እናውቃለን።
[32] ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይኖች ያበራ አልተሰማም።
[33] ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባልቻለም ነበር።”
[34] እነርሱም መልሰው ፥ “ራስህ በኀጢኣት የተወለድህ አንተ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት፤ ወደ ውጭም አወጡት።
[35] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ አገኘውምና ፥ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው።
[36] ያ ሰውም ፥ “አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?” ብሎ መለሰለት።
[37] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው ” አለው።
[38] እርሱም ፥ “አቤቱ፥ አምናለሁ ” ብሎ ሰገደለት።
[39] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፥ የሚያዩትም እንዲታወሩ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቻለሁ ” አለው።
[40] ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሲናገር ሰምተው ፥ “እኛ ደግሞ ዕዉሮች ነን?” አሉት።
[41] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ዕዉሮችስ ብትሆኑ ኀጢኣት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ትላላችሁ፤ አታዩምም፤ ስለዚህም ኀጢኣታችሁ ጸንቶ ይኖራል ” አላቸው።