[1] “ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ።
[2] በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር።
[3] ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተም እኔ በአለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ።
[4] ወዴትም እንደምሄድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ መንገዱንም ታውቃላችሁ።”
[5] ቶማስም ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ የምትሄድበትን የማናውቅ እንግዲህ መንገዱን እንዴት እናውቃለን?” አለው።
[6] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
[7] እኔንስ ብታውቁኝ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን አውቃችሁታል፤ አይታችሁትማል።”
[8] ፊልጶስም ፥ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል ” አለው።
[9] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን አብሬአችሁ ስኖር አታወቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ እንግዲህ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ?
[10] እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርሁት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ።
[11] እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ።
[12] “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።
[13] አብ በወልድ ይከብር ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ።
[14] በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።
[15] “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ።
[16] እኔም አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይልክላችኋል።
[17] እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ይኖራልና፤ ያድርባችሁማልና።
[18] “የሙት ልጆች ትሆኑ ዘንድ አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
[19] ገና ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና፤ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ።
[20] እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ፥ እናንተም በእኔ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ ያንጊዜ ታውቃላችሁ።
[21] ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለ የሚጠብቀውም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
[22] የአስቆሮቱ ሰው ያይደለ ይሁዳም ፥ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ያይደለ ለእኛ ራስህን ትገልጥ ዘንድ እንዳለህ የተናገርኸው ምንድን ነው?” አለው።
[23] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው ፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን።
[24] የማይወደኝ ግን ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህም የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ቃል ነው እንጂ የእኔ ቃል አይደለም።
[25] “ከእናንተም ጋር ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ።
[26] ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።
[27] “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፤ አትፍሩም።
[28] እኔ እንደምሄድ ወደ እናንተም እንደምመለስ የነገርኋችሁን ሰምታችኋል፤ ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ እርሱ አብ ይበልጠኛልና።
[29] አሁንም ይህ በሆነ ጊዜ ታምኑ ዘንድ አስቀድሜ ሳይሆን ነገርኋችሁ።
[30] እንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና፤ በእኔም ላይ ምንም አያገኝም።
[31] ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ትእዛዙን እንደ ሰጠኝ እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ተነሡ ከዚህ፤ እንሂድ።