[1] ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበረ፤ ወደ ይሁዳ ምድርም ሊሄድ አልወደደም፤ አይሁድ ሊገድሉት ይሹ ነበርና።
[2] የአይሁድም የዳስ በዓላቸው ደርሶ ነበር።
[3] ወንድሞቹም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አሉት፥ “ደቀ መዛሙርትህ የምትሠራውን ሥራህን እንዲያዩ ከዚህ ወጥተህ ወደ ይሁዳ ሀገር ሂድ።
[4] ሊገለጥ ወድዶ ሳለ በስውር አንዳች ነገር የሚያደርግ ማንም የለምና፤ አንተ ግን ይህን የምታደርግ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ።
[5] ወንድሞቹ ገና አላመኑበትም ነበርና።
[6] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተዘጋጀ ነው።
[7] ዓለም እናንተን ሊጠላችሁ አይችልም፤ እኔን ግን ይጠላኛል፤ ሥራዉ ክፉ እንደ ሆነ እኔ እመሰክርበታለሁና።
[8] እናንተም ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔ አሁን ወደዚህ በዓል አልወጣም፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና።”
[9] እርሱም እንዲህ ብሎአቸው በገሊላ ቀረ።
[10] ወንድሞቹ ለበዓል ከወጡ በኋላ፥ እርሱም ያንጊዜ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ።
[11] አይሁድም ፥ “ያ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ጀመር።
[12] ሕዝቡም ስለ እርሱ ብዙ አንጐራጐሩ ፥ “ደግ ሰው ነው ” ያሉ ነበሩ፤ ሌሎች ግን ፥ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ ” አሉ።
[13] ነገር ግን፥ አይሁድን በመፍራት የእርሱን ነገር ገልጦ የተናገረ አልነበረም።
[14] በበዓሉ ቀኖች እኩሌታም ጌታችን ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመረ።
[15] አይሁድም ፥ “ይህ ሳይማር መጽሐፍን እንዴት ያውቃል?” እያሉ ትምህርቱን አደነቁ።
[16] ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ትምህርቴ የላከኝ ናት እንጂ የእኔ አይደለችም።
[17] ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል።
[18] ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይሻል፤ የላከውን ያከብር ዘንድ የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም።
[19] ሙሴ ኦሪትን ሰጥቶአችሁ የለምን? ከእናንተ አንዱ ስንኳ ኦሪትን የሚያደርግ የለም፤ እንግዲህ ልትገድሉኝ ለምን ትሻላችሁ?”
[20] ሕዝቡም ፥ “ጋኔን አለብህን? ማን ሊገድልህ ይሻል?” ብለው መለሱለት።
[21] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው ፥ “አንድ ሥራ ሠራሁ፤ ሁላችሁም አደነቃችሁ።
[22] ስለዚህ ሙሴ ግዝረትን ሰጥቶአችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከአባቶች ናት እንጂ ከሙሴ አይደለችም፤ በሰንበትም ሰውን ትገዝሩታላችሁ።
[23] የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት የሚገዘር ከሆነ እንግዲያ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ባድነው ለምን ትነቅፉኛላችሁ?
[24] የእውነት ፍርድ ፍረዱ እንጂ ለሰው ፊት በማድላት አትፍረዱ።”
[25] ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዲህ የሚሉ ነበሩ ፥ “ይህ አይሁድ ሊገድሉት የሚሹት አይደለምን?
[26] እነሆ፥ እርሱ በገሀድ ይናገራል፤ እነርሱ ግን ምንም የሚሉት የለም፤ ይህ በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ ምናልባት አለቆች ዐውቀው ይሆን?
[27] ነገር ግን ይህን ከየት እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜስ ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም”።
[28] ጌታችን ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር ቃሉን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ ፥ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔ ራሴ የመጣሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ አለ።
[29] እኔ ግን አውቀዋለሁ፤ እኔ ከእርሱ ነኝና፥ እርሱም ልኮኛልና።
[30] ስለዚህም ሊይዙት ወደው ነበር፤ ነገር ግን እጁን በእርሱ ላይ ያነሣ የለም፤ ጊዜዉ ገና አልደረሰም ነበርና።
[31] ከሕዝቡም ብዙዎች አመኑበትና ፥ “በውኑ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው ተአምራት የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ።
[32] ፈሪሳውያንም ሕዝቡ በእርሱ ምክንያት እንደ አጕuረመረሙ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ ሎሌዎቻቸውን ላኩ።
[33] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “ጥቂት ቀን አብሬአችሁ እኖራለሁ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ።
[34] ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበትም እናንተ መምጣት አትችሉም።”
[35] አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ ፥ “እኛ ልናገኘው የማንችል ይህ ወዴት ይሄዳል? ወይስ የግሪክን ሰዎች ለማስተማር በግሪክ ሀገር ወደ ተበተኑት ይሄዳልን?
[36] ‘ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አትችሉም ’ የሚለን ይህ ነገር ምንድን ነው?”
[37] በኋለኛዪቱ በታላቅዋ የበዓል ቀንም ጌታችን ኢየሱስ ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ ፥ “የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።
[38] በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደ ተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈስሳል።”
[39] ይህንም የሚያምኑበት ሰዎች ይቀበሉት ዘንድ ስለ አላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፤ ጌታችን ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና።
[40] ከሕዝቡም ብዙ ሰዎች ይህን ነገር ሰምተው “በእውነት ይህ ነቢይ ነው ” አሉ።
[41] “ክርስቶስ ነው ” ያሉም አሉ፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አሉ ፥ “በውኑ ክርስቶስ ከገሊላ ይወጣልን?
[42] መጽሐፍ ‘ክርስቶስ ከዳዊት ዘርና ከዳዊት ከተማ ከቤተ ልሔም ይመጣል ’ ይል የለምን?”
[43] ስለ እርሱም ሕዝቡ እርስ በርሳቸው ተለያዩ።
[44] ከእነርሱም ሊይዙት የወደዱ ነበሩ፤ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጁን ያነሣ የለም።
[45] ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመለሱ፤ እነርሱም ፥ “ያላመጣችሁት ለምንድን ነው?” አሉአቸው።
[46] ሎሌዎቻቸውም መልሰው ፥ “ያ ሰው እንደ ተናገረው ያለ ከቶ ሰው አልተናገረም ” አሉአቸው።
[47] ፈሪሳውያንም መልሰው እንዲህ አሉአቸው ፥ “እናንተም ደግሞ ተሳሳታችሁን?
[48] ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን ያመነበት አለን?
[49] ኦሪትን ከማያውቁ ከእነዚህ ስሑታን ሕዝብ በቀር፤ እነርሱም የተረገሙ ናቸው።”
[50] ከእነርሱም አንዱ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ የሄደው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው።
[51] “ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ፤ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?”
[52] እነርሱም መልሰው ፥ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሣ መርምርና እይ ” አሉት።
[53] ሁሉም እያንዳንዳቸው ወደ ቤታቸው ሄዱ።