[1] ከዚህም በኋላ ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስን ይዞ ገረፈው።
[2] ጭፍሮችም የእሾህ አክሊል ጐንጕuነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም አለበሱት።
[3] ወደ እርሱም እየመጡ ፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ” ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር።
[4] ጲላጦስም እንደገና ወደ ውጭ ወጣና ፥ “እነሆ፥ በእርሱ ላይ አንዲት በደል ስንኳን ያገኘሁበት እንደሌለ ታውቁ ዘንድ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ ” አላቸው።
[5] ጌታችን ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ፤ ጲላጦስም ፥ “እነሆ፥ ሰውዬው ” አላቸው።
[6] ሊቃነ ካህናትና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ ፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ፤ ጲላጦስም ፥ “እናንተ ራሳችሁ ውሰዱና ስቀሉት፤ እኔስ በእርሱ ላይ በደል አላገኘሁበትም ” አላቸው።
[7] አይሁድም መልሰው ፥ “እኛ ሕግ አለን፤ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባል፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና ” አሉት።
[8] ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ፈራ።
[9] ደግሞም ወደ ፍርድ አደባባይ ገባና ጌታችን ኢየሱስን ፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።
[10] ጲላጦስም ፥ “ለእኔም አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ፥ አታውቅምን?” አለው።
[11] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ታላቅ ኀጢኣት አለበት ” አለው።
[12] ስለዚህም ጲላጦስ ሊፈታው ወድዶ ነበር፤ አይሁድ ግን ፥ “ይህን ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ በቄሣር ላይ የሚያምፅ ነውና ” ብለው ጮሁ።
[13] ጲላጦስም ይህን ሰምቶ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ ተብሎ በሚጠራው “ጸፍጸፍ ” በሚሉት ቦታ ላይ በወንበር ተቀመጠ።
[14] የፋሲካም የመዘጋጀት ቀን ነበር፤ ጊዜዉም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ ጲላጦስም አይሁድን ፥ “እነሆ፥ ንጉሣችሁ ” አላቸው፤
[15] እነርሱ ግን ፥ “አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ። ጲላጦስም ፥ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው፤ ሊቃነ ካህናቱም ፥ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ” ብለው መለሱ።
[16] ከዚህ በኋላ ሊሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጌታችን ኢየሱስንም ተቀብለው ወሰዱት።
[17] መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ።
[18] በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር አንዱን በቀኝ፥ አንዱንም በግራ አድርገው ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችን ሰቀሉ፤ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ።
[19] ጲላጦስም ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረ፤ ጽሕፈቱም ፥ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ” የሚል ነበር።
[20] ከአይሁድም ይህቺን ጽሕፈት ያነበብዋት ብዙዎች ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስን የሰቀሉበት ቦታ ለከተማ ቅርብ ነበርና፤ ጽሕፈቱም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በሮማይስጥና በግሪክ ነበር።
[21] ሊቃነ ካህናትም ጲላጦስን አሉት ፥ “እርሱ ራሱ ‘እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ’ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ።”
[22] ጲላጦስም ፥ “የጻፍሁትን ጻፍሁ ” ብሎ መለሰላቸው።
[23] ጭፍሮችም ጌታችን ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ከጭፍሮቹ ለእያንዳንዱ አራት ክፍል አድርገው መደቡት፤ ቀሚሱንም ወሰዱ፤ ቀሚሱም ከላይ ጀምሮ የተሠራ ሥረወጥ እንጂ የተሰፋ አልነበረም።
[24] እርስ በርሳቸውም ፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰ ይድረሰው እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፤” ይህም “ልብሶቼን ለራሳቸው ተካፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ጭፍሮችም እንዲሁ አደረጉ።
[25] በጌታችን በኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊት ማርያምም ቆመው ነበር።
[26] ጌታችን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን ፥ “አንች ሆይ፥ እነሆ፥ ልጅሽ ” አላት።
[27] ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን ፥ “እናትህ እነኋት ” አለው፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
[28] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ ” አለ።
[29] በዚያም ሆምጣጤ የመላበት ማሰሮ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በስምዛ ዘንግ ከአፉ አገናኝተው ጨመቁት።
[30] ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ ፥ “ሁሉ ተፈጸመ ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ።
[31] አይሁድ ግን የመዘጋጀት ቀን ነበርና፥ የዚያች ሰንበትም ቀን ታላቅ ናትና “ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ አይደር ” አሉ፤ ጭን ጭናቸውንም ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት።
[32] ጭፍሮችም መጥተው ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትን የአንደኛውንና የሁለተኛውን ጭኖች ሰበሩ።
[33] ወደ ጌታችን ኢየሱስም ሄደው ፈጽሞ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ጭኑን አልሰበሩም።
[34] ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ የቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ያንጊዜም ከእርሱ ደምና ውኃ ወጣ።
[35] ያየውም መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እርሱም እናንተ ልታምኑ እውነት እንደሚናገር ያውቃል።
[36] ይህ ሁሉ የሆነው “ከእርሱ ዐፅሙን አትስበሩ ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
[37] ሌላዉም መጽሐፍ ደግሞ “ የወጉትን ያዩታል ” ይላል።
[38] ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለፈራ በስውር የጌታችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያስ ሰው ዮሴፍ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ይወስድ ዘንድ ጲላጦስን ለመነው፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። እርሱም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ።
[39] ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀብሩበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ።
[40] እንደ አይሁድ አገናነዝ ሥርዐትም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወስደው ከሽቱ ጋር በበፍታ ገነዙት።
[41] በዚያም በተሰቀለበት ቦታ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በዚያ የአትክልት ስፍራ ውስጥም በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር።
[42] ጌታችን ኢየሱስንም በዚያ ቀበሩት፤ ለአይሁድ የመሰናዳት ቀን ነበርና፤ መቃብሩም ለሰቀሉበት ቦታ ቅርብ ነበር።