[1] የማርያምና የእኅቷ የማርታ መንደር በሚሆን በቢታንያ ስሙ አልዓዛር የሚባል የታመመ አንድ ሰው ነበር።
[2] ማርያም ግን ጌታችንን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጕuርዋ ያሸችው ናት፤ ወንድምዋ አልዓዛርም ታሞ ነበር።
[3] እኅቶቹም ፥ “ጌታችን ሆይ፥ እነሆ፥ የምትወደው ታሞአል ” ብለው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ላኩ።
[4] ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አለ ፥ “ይህ ደዌ በእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም።”
[5] ጌታችን ኢየሱስም ማርታንና እኅቷን ማርያምን፥ አልዓዛርንም ይወዳቸው ነበር።
[6] እንደ ታመመ በሰማ ጊዜM በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ።
[7] ከዚህም በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱን ፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እንሂድ ” አላቸው።
[8] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ሊወግሩህ ይሹ አልነበረምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደዚያ ልትሄድ ትሻለህን?” አሉት።
[9] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚሄድ አይሰናከልም፤ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና።
[10] በሌሊት የሚሄድ ግን ይሰነካከላል፤ በውስጡ የሚያየው ብርሃን የለምና።”
[11] ይህንም ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፤ ከዚህም በኋላ ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ ” አላቸው።
[12] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም ” አሉት።
[13] ጌታችን ኢየሱስም ስለ ሞቱ ተናገረ፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት መስሎአቸው ነበር።
[14] ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ገልጦ እንዲህ አላቸው ፥ “አልዓዛር ሞተ።
[15] ታምኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ።”
[16] ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስም፥ ባልንጀሮቹን ደቀ መዛሙርት ፥ “እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ ” አላቸው።
[17] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ፤ ከዚያም በደረሰ ጊዜ ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው።
[18] ቢታንያም ለኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ቅርብ ነበረች።
[19] ከአይሁድም ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርያምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙዎች ነበሩ።
[20] ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር።
[21] ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር።
[22] አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።”
[23] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ወንድምሽስ ይነሣል ” አላት።
[24] ማርታም ፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ ” አለችው።
[25] ጌታችን ኢየሱስም አላት ፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል።
[26] ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?”
[27] እርስዋም ፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ ” አለችው።
[28] ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና ፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል ” አለቻት።
[29] እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች።
[30] ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር።
[31] ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት።
[32] ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር ” አለችው።
[33] ጌታችን ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋ ጋር የመጡ አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ።
[34] እርሱም ፥ “የት ቀበራችሁት?” አለ፤ እነርሱም ፥ “አቤቱ፥ መጥተህ እይ ” አሉት።
[35] ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።
[36] አይሁድም ፥ “ምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ ” አሉ።
[37] ከእነርሱም መካከል ፥ “ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይን ያበራው ይህ ሰው ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበርን?” ያሉ ነበሩ።
[38] ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ ወደ መቃብሩም ሄደ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበር፤ በላዩም ታላቅ ድንጋይ ተገጥሞበት ነበር።
[39] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ድንጋዩን አንሡ ” አላቸው፤ የሟቹ እኅት ማርታም ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆናል ” አለችው።
[40] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ብታምናስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?” አላት።
[41] ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
[42] እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ።”
[43] ይህንም ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸና ፥ “አልዓዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ ” አለ።
[44] ሞቶ የነበረውም እንደ ተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ ” አላቸው።
[45] ስለዚህ ከአይሁድም ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን አይተው በእርሱ አመኑ።
[46] ከእነርሱም መካከል ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውንም ሁሉ ነገሩአቸው።
[47] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው ፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ያደርጋል፤ ምን እናድርግ?
[48] እንዲሁ ብንተወውም ሁሉ ያምኑበታል፤ የሮም ሰዎችም መጥተው ሀገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል።”
[49] በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተስ ምንም አታውቁም።
[50] ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል።”
[51] ይህንም ከልቡ የተናገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝብ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ።
[52] ስለ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ።
[53] ከዚያችም ቀን ጀምሮ የካህናት አለቆች ሊገድሉት ተማከሩ።
[54] ከዚያም ወዲያ ጌታችን ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጥ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ለምድረ በዳ አቅራቢያ ወደ ሆነች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።
[55] የአይሁድም የፋሲካ በዓል ቀርቦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ከበዓሉ አስቀድሞ ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከየሀገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ነበር።
[56] አይሁድም ጌታችን ኢየሱስን ይፈልጉት ጀመር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው ፥ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓል አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ።
[57] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ያለበትን የሚያውቅ ቢኖር ይይዙት ዘንድ እንዲያመለክታቸው አዘዙ።