[1] ከሳምንቱም በመጀመሪያዉ ቀን ማርያም መግደላዊት በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩንም ከመቃብሩ አፍ ተነሥቶ አገኘችው።
[2] ፈጥናም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ጌታችን ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደዚያ ወደ ሌላዉ ደቀ መዝሙር መጥታ ፥ “ጌታዬን ከመቃብር ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም ” አለቻቸው።
[3] ጴጥሮስና ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙርም ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።
[4] ሁለቱም በአንድነት ሲሮጡ ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞት ወደ መቃብሩ ደረሰ።
[5] ጐንበስ ብሎም ሲመለከት በፍታዉን ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ አልገባም።
[6] ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤
[7] በፍታዉንም በአንድ ወገን ተቀምጦ አየ፤ በራሱ ላይ የነበረው መጠምጠሚያም ሳይቃወስ ለብቻው ተጠቅልሎ አየ፤ ከበፍታዉ ጋርም አልነበረም።
[8] ከዚህም በኋላ አስቀድሞ ወደ መቃብሩ የደረሰው ሌላዉ ደቀ መዝሙር ገባ፤ አይቶም አመነ፤
[9] ከሙታን ተለይቶ ይነሣ ዘንድ እንደ አለው በመጻሕፍት የተጻፈውን ገና አላወቁም ነበርና።
[10] ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ ቤታቸው ገቡ።
[11] ማርያም ግን ከመቃብሩ በስተውጭ እያለቀሰች ቆማ ነበረ፤ እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ጐንበስ ብላ ተመለከተች።
[12] ሁለት መላእክትንም ነጭ ልብስ ለብሰው የጌታችን የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ አንዱ በራስጌ፥ አንዱም በግርጌ ተቀምጠው አየች።
[13] እነዚያ መላእክትም ፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል?” አሉአት፤ እርስዋም ፥ “ጌታዬን ከመቃብር ውስጥ ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም ” አለቻቸው።
[14] ይህንም ተናግራ ወደ ኋላዋ መለስ ስትል ጌታችን ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ጌታችን ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
[15] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል? ማንንስ ትሺያለሽ?” አላት፤ እርስዋ ግን የአትክልት ቦታ ጠባቂ መስሎአት ፥ “ጌታዬ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ ሄጄ ወደ እኔ እንዳመጣውና ሽቱ እንድቀባው ወዴት እንደ አኖርኸው ንገረኝ ” አለችው።
[16] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ማርያም!” አላት፤ እርስዋም መለስ ብላ በዕብራይስጥ ቌንቌ ፥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜዉም “መምህር ” ማለት ነው።
[17] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ፥ ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ፥ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው ” አላት።
[18] ማርያም መግደላዊትም ሄደች፤ ጌታን እንደ አየች፥ ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረቻቸው።
[19] ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቈልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን ” አላቸው።
[20] ይህንም ብሎ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው።
[21] ጌታችን ኢየሱስም ዳግመኛ እንዲህ አላቸው ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ።”
[22] ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
[23] ኀጢኣታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም።”
[24] ጌታችን ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ዲዲሞስ የሚሉት ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቶማስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም።
[25] ሌሎች ደቀ መዛሙርትም ፥ “ጌታችንን አየነው ” አሉት፤ እርሱ ግን ፥ “የችንካሩን ምልክት በእጁe ካላየሁ፥ ጣቴንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርሁ፥ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም ” አላቸው።
[26] ከስምንት ቀን በኋላም ዳግመኛ ደቀ መዛሙርቱ በውስጡ ሳሉ፥ ቶማስም አብሮአቸው ሳለ በሩ እንደ ተዘጋ ጌታችን ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆመና ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን ” አላቸው።
[27] ከዚህም በኋላ ቶማስን፥ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን ” አለው።
[28] ቶማስም ፥ “ጌታዬ አምላኬም ” ብሎ መለሰ።
[29] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ስለ አየኸኝ አመንህን? ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው ” አለው።
[30] ጌታችን ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ሌላ ተአምራት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ።
[31] ነገር ግን ይህ የተጻፈ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ነው።