[1] ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ።
[2] በዚያም ምሳ አደረጉለት፤ ማርታም ታሳልፍላቸው ነበር፤ አብረውት ምሳ ከበሉትም አንዱ አልዓዛር ነበር።
[3] ማርያም ግን ዋጋዉ የከበረና የበዛ አንድ ነጥር የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ወሰደችና የጌታችን ኢየሱስን እግር ቀባችው፤ በፀጕuሯም አሸችው፤ የዚያ ሽቱ መዓዛም ቤቱን መላው።
[4] ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የነበረ ያሲዘው ዘንድ ያለው የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን እንዲህ አለ።
[5] “ለነዳያን ይሰጥ ዘንድ ይህን ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ለምን አልሸጡትም?”
[6] ይህንም ያለ፥ ድሆች አሳዝነውት አይደለም፤ ሌባ ነበርና፥ ሙዳየ ምጿቱንም ሲጠብቅ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ነበርና ስለዚህ ነው እንጂ።
[7] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ ፥ “ለምቀበርበት ቀን ትጠብቀው ዘንድ ተዉአት።
[8] ድሆች ግን ዘወትር አብረዋችሁ አሉ፤ ዘወትርም ታገኙአቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ መልካም ታደርጉላቸዋላችሁ፤ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም።”
[9] ከአይሁድም ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ በዚያ እንዳለ በዐወቁ ጊዜ ወደ እርሱ መጡ፤ የመጡትም ጌታችን ኢየሱስን ለማየት ብቻ አልነበረም፤ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ለይቶ ያስነሣዉን አልዓዛርንም ያዩ ዘንድ ነበር እንጂ።
[10] የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ሊገድሉት ተማከሩ።
[11] ከአይሁድ ብዙዎች ስለ እርሱ እየሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።
[12] በማግሥቱም ለበዓል መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰሙ ጊዜ፥
[13] የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ፥ የእስራኤልም ንጉሥ ቡሩክ ነው ” እያሉ ወጥተው ተቀበሉት።
[14] ጌታችን ኢየሱስም የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርስዋ ላይ ተቀመጠ።
[15] “የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ይመጣል ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
[16] ደቀ መዛሙርቱም አስቀድመው ይህን ነገር አላወቁም፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያ ጊዜ ይህ ነገር ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ፥ ይህንም እንደ አደረጉለት ትዝ አላቸው።
[17] ከዚያም አብረውት የነበሩት ሕዝብ አልዓዛርን ከመቃብር እንደ ጠራው፥ ከሙታንም እንደ አስነሣው መሰከሩለት።
[18] ስለዚህም ነገር ሕዝቡ ሁሉ ሊቀበሉት ወጡ፤ ይህን ተአምራት እንደ አደረገ ሰምተዋልና።
[19] ፈሪሳውያንም እርስ በርሳቸው ፥ “የምታገኙት ምንም ጥቅም እንደሌለ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለም ሁሉ ተከትሎታል ” ተባባሉ።
[20] ከጽርዕ ሰዎችም ይሰግዱ ዘንድ ለበዓል የወጡ ነበሩ።
[21] እነርሱም ከገሊላ፥ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ሄደው ፥ “አቤቱ፥ ጌታ ኢየሱስን ልናየው እንወድዳለን ” ብለው ለመኑት።
[22] ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስም ሄደው ለጌታችን ለኢየሱስ ነገሩት።
[23] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁን የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ጊዜው ደረሰ።
[24] እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች።
[25] ነፍሱን የሚወዳት ይጥላታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጥላትም ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል።
[26] እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።
[27] “አሁንስ ነፍሴ ታወከች፤ ግን ምን እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚች ሰዓት ነፍሴን አድናት፤ ነገር ግን ስለዚህ ነገር ለዚች ሰዓት ደርሻለሁ።
[28] አባት ሆይ፥ ልጅህን አክብረው።” ከሰማይም ፥ “አከበርሁህ፤ ደግሞም እንደገና አከብርሃለሁ፤” የሚል ቃል መጣ።
[29] በዚያ ቆመው ይሰሙ የነበሩ ሕዝብ ግን “ነጐድጓድ ነው ” አሉ፤ “መልአክ ተናገረው ” ያሉም አሉ።
[30] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ይህ ቃል የመጣ ስለ እናንተ ነው እንጂ ስለ እኔ አይደለም።
[31] አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደረሰ፤ ከእንግዲህስ ወዲህ የዚህን ዓለም ገዥ ወደ ውጭ አስወጥተው ይሰዱታል።
[32] እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።”
[33] ይህንም ያለ በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ነው።
[34] ሕዝቡም ፥ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር በኦሪት ሰምተን ነበር፤ እንግዲህ እንዴት አንተ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ አለው ’ ትለናለህ? እንግዲህ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት።
[35] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “ ገና ለጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው፤ በጨለማ የሚመላለስ የሚሄድበትን አያውቅምና ጨለማ እንዳያገኛችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤
[36] የብርሃን ልጆች ትሆኑ ዘንድ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ ” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ተሰወራቸውም።
[37] ይህንም ያህል ተአምራት በፊታቸው ሲያደርግ አላመኑበትም።
[38] “አቤቱ፥ ምስክርነታችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ያለው የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል ይደርስ ዘንድ።
[39] ስለዚህም ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ ዳግመኛ እንዲህ ብሎአልና።
[40] “በዐይናቸው አይተው፥ በልባቸውም አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው ዐይኖቻቸው ታወሩ፤ ልባቸውም ደነደነ።”
[41] ኢሳይያስ ጌትነቱን አይቶአልና፥ ይህን ተናገረ፤ ስለ እርሱም መሰከረ።
[42] ከሕዝቡ አለቆችም ያመኑበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምኵuራብ አስወጥተው እንዳይሰዱአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም።
[43] ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።
[44] ጌታችን ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ ፥ “በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም።
[45] እኔን ያየ የላከኝን አየ።
[46] በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣሁ።
[47] ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድበት አልመጣሁምና።
[48] የሚክደኝን፥ ቃሌንም የማይቀበለውን ግን የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻዪቱ ቀን ይፈርድበታል።
[49] የተናገርሁት ከእኔ የሆነ አይደለምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እንድናገር፥ እንዲህም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ።
[50] ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ እኔም የምናገረውን አብ እንዳለኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”