[1] ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ወደ ጥብርያዶስ ሄደ።
[2] በበሽተኟችም ላይ ያደረገውን ተአምራት ስለ አዩ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤
[3] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር በዚያ ተቀመጠ።
[4] የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ቀርቦ ነበር።
[5] ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ሲመጡ አየና ፊልጶስን ፥ “ለእነዚህ ሰዎች የምናበላቸው እንጀራ ከወዴት እንግዛ?” አለው።
[6] ሲፈትነው ይህን አለ እንጂ፥ እርሱስ የሚያደርገውን ያውቅ ነበር።
[7] ፊልጶስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “ከእነርሱ ለእያንዳንዱ ጥቂት ጥቂት ይወስዱ ዘንድ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም።”
[8] ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፥
[9] “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህ ይህን ለሚያህል ሰው ምን ይበቃሉ?”
[10] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ ” አለ፤ የዚያ ቦታም ሣሩ ብዙ ነበር፤ ወንዶቹም በመስኩ ላይ ተቀመጡ፤ ቐጥራቸውም አምስት ሺህ ያህል ነበር።
[11] ጌታችን ኢየሱስም ያን እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤ ከዓሣውም እንዲሁ የፈለጉትን ያህል ሰጡአቸው።
[12] ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ፥ “ከቐርስራሹ ምንም የሚወድቅ እንዳይኖር የተረፈውን ቐርስራሽ አንሡ፤” አላቸው።
[13] እነርሱም ሰበሰቡ፥ በልተው ከጠገቡ በኋላም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈው ቐርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ።
[14] ሕዝቡም ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን ተአምራት አይተው ፥ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው ” አሉ።
[15] ጌታችን ኢየሱስም መጥተው ነጥቀው ሊያነግሡት እንደሚሹ ዐወቀባቸውና ብቻውን ወደ ተራራ ሄደ።
[16] በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ።
[17] ወደ ታንኳም ወጡ፤ ወደ ባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆምም ሄዱ፤ እነሆም፥ ፈጽሞ ጨለማ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ እነርሱ ገና አልመጣም ነበር።
[18] ባሕሩ ግን ይታወክ ነበር፤ ጽኑ ነፋስ ይነፍስ ነበርና።
[19] ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ያህል ከሄዱ በኋላ ጌታችን ኢየሱስን በባሕር ላይ ሲሄድ አዩት፤ ወደ ታንኳዉ በቀረበ ጊዜም ፈሩ።
[20] እርሱም ፥ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ ” አላቸው።
[21] ወደ ታንኳውዪቱ ሊያወጡት ሲሹም ታንኳዪቱ ወዲያውኑ ሊሄዱ ወደ ወደዱበት ወደብ ደረሰች።
[22] በማግሥቱም ከባሕሩ ዳር ቆመው የነበሩ ሰዎች ከአንዲት ታንኳ በቀር ከዚያ ሌላ ታንኳ እንዳልነበረ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሄዱ እንጂ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ እንዳልወጣ አዩ።
[23] ደግሞም ጌታችን የባረከውን እንጀራ ከበሉበት ቦታ አቅራቢያ ከጥብርያዶስ ሌሎች ታንኳዎች መጥተው ነበር።
[24] እነዚያ ሰዎችም ጌታችን ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱም በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስን ይፈልጉት ዘንድ በእነዚያ ታንኳዎች ገብተው ወደ ቅፍርናሆም መጡ።
[25] በባሕሩ ዳርም ባገኙት ጊዜ ፥ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት።
[26] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስለ አያችሁ አይደለም።
[27] የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።”
[28] “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንሠራ ዘንድ ምን እናድርግ?” አሉት።
[29] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ ነው፤” አላቸው።
[30] እነርሱም እንዲህ አሉት ፥ “የምትሠራውን አይተን በአንተ እናምን ዘንድ ምን ተአምራት ታደርጋለህ?
[31] አባቶቻችንስ ‘ሊበሉ እንጀራ ከሰማይ ሰጣቸው ’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በምድረ በዳ መና በሉ።
[32] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ያን እንጀራ ከሰማይ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ከሰማይ የእውነት እንጀራን ሰጥቶአችኋል እንጂ።
[33] የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።”
[34] እነርሱም ፥ “አቤቱ ከዚያ እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን ” አሉት።
[35] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም ለዘለዓለም አይጠማም።
[36] ነገር ግን እላችኋለሁ፤ አያችሁኝ፤ አላመናችሁብኝምም።
[37] አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም።
[38] ከሰማይ የወረድሁ የላከኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃዴን ላደርግ አይደለምና።
[39] የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።
[40] የአባቴ ፈቃዱ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ የሚያምንበት ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።”
[41] አይሁድም ስለ እርሱ አንጐራጐሩ፤ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ” ብሎአቸዋልና።
[42] “እኛ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?” አሉ።
[43] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕuሩ።
[44] የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣትን የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።
[45] ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ ’ ተብሎ በነቢያት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአባቴ የሰማ ሁሉ ተምሮ ወደ እኔ ይመጣል።
[46] ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር አብን ያየው ማንም የለም፤ እርሱም አብን አየው።
[47] እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው።
[48] የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።
[49] አባቶቻችሁስ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም።
[50] ከእርሱ የበላ ሁሉ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው።”
[51] “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ እንጀራ ሥጋዬ ነው።”
[52] አይሁድም ፥ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።
[53] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም።
[54] ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛዪቱ ቀን አነሣዋለሁ።
[55] ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።
[56] ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ።
[57] የላከኝ አብ ሕያው እንደ ሆነ፥ እኔም ስለ አብ ሕያው ነኝ፤ ሥጋዬንም የሚበላ እርሱ ደግሞ ስለ እኔ ሕያው ሆኖ ይኖራል።
[58] ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተውት እንደሞቱበት ያለ መና አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል።”
[59] በቅፍርናሆምም በምኵuራብ ሲያስተምራቸው ይህን ተናገረ፤
[60] ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ ይህን ሰምተው ፥ “ይህ ነገር የሚያስጨንቅ ነው፤ ማንስ ሊሰማው ይችላል?” አሉ።
[61] ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ አንጐራጐሩ በልቡ ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው ፥ “ይህ ያሰናክላችኋልን?
[62] እንግዲህ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲያርግ ብታዩት እንዴት ይሆን?
[63] ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ግን አንዳች አይጠቅምም፤ ይህም እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው።
[64] ነገር ግን ከእናንተ ውስጥ የማያምኑ አሉ፤” ጌታችን ኢየሱስ ከጥንት ጀምሮ የማያምኑበት እነማን እንደ ሆኑ፥ የሚያሲዘውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና።
[65] እንዲህም አላቸው ፥ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ከአብ ካልተሰጠው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚቻለው የለም።”
[66] ስለዚህም ከደቀ መዛሙርቱ ወደ ኋላቸው የተመለሱ ብዙዎች ናቸው፤ ከዚያም ወዲህ አብረውት አልሄዱም።
[67] ጌታችን ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ፥ “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትሻላችሁን?” አላቸው።
[68] ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “አቤቱ፥ የዘለዓለም የሕይወት ቃል እያለህ ወደ ማን እንሄዳለን?
[69] እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንደ ሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም።”
[70] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እኔ እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጫችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ሰይጣን ነው።”
[71] ይህንም ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮታዊው ይሁዳ ተናገረ፤ እርሱ ያሲዘው ዘንድ አለውና፤ እርሱም ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ነበር።