[1] በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
[2] ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።
[3] ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም።
[4] ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤
[5] ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላገኘውም።
[6] ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር።
[7] እርሱም ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምን ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ።
[8] ስለ ብርሃን ምስክር ሊሆን መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም።
[9] ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው።
[10] በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም።
[11] ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም።
[12] ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው።
[13] እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም።
[14] ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው።
[15] ምስክሩ ዮሐንስ ስለ እርሱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፤ እንዲህም አለ ፥ “እኔ ስለ እርሱ ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ በኋላ ይመጣል ያልኋችሁ ሰው ይህ ነው፥ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበረና።”
[16] እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀበልን።
[17] ኦሪት በሙሴ ተሰጥታን ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን።
[18] በአባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ገለጠልን እንጂ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያየው የለም።
[19] አይሁድ ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ይጠይቁት ዘንድ ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም በላኩ ጊዜ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።
[20] እርሱም ፥ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ” ብሎ አመነ እንጂ አልካደም።
[21] “እንኪያ አንተ ማነህ? አንተ ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት፤ “አይደለሁም ” አለ፤ “እንኪያ አንተ ነቢዩ ነህን?” አሉት፤ “አይደለሁም ” አለ።
[22] “እንኪያስ አንተ ማነህ? ለላኩንም መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ማን ትላለህ?” አሉት።
[23] እርሱም ፥ “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ እያለ በምድረ በዳ የሚሰብክ የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እኔ ነኝ ” አለ።
[24] የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ።
[25] “እንኪያስ ክርስቶስን ካልሆንህ፥ ኤልያስንም ካልሆንህ፥ ነቢይንም ካልሆንህ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት።
[26] ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል።
[27] ከእኔ በኋላ የሚመጣው፥ ከእኔ በፊት የነበረው፥ የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኳ የማይገባኝ ነው።”
[28] ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ እንዲህ ሆነ።
[29] በማግሥቱም ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
[30] ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና።
[31] እኔ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል እንዲያውቁት ስለዚህ እኔ በውኃ ላጠምቅ መጣሁ።”
[32] ዮሐንስም ምስክርነቱን እንዲህ ብሎ ተናገረ ፥ “መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ እንደ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየሁ።
[33] እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
[34] እኔም ራሴ አይቻለሁ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ ምስክሩ ነኝ።”
[35] በማግሥቱም ደግሞ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ሳለ፥
[36] ጌታችን ኢየሱስን ሲሄድ አይቶ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ” አለ።
[37] ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ ሲል ሰምተው ጌታችን ኢየሱስን ተከተሉት።
[38] ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና ፥ “ምን ትሻላችሁ?” አላቸው።
[39] እነርሱም ፥ “ረቢ፥ ትርጓሜውም መምህር ሆይ፥ ማለት ነው፤ ወዴት ትኖራለህ?” አሉት።
[40] እርሱም “መጥታችሁ እዩ ” አላቸው፤ ሄደውም የሚኖርበትን አዩ፤ ያን ዕለትም እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ በእርሱ ዘንድ ዋሉ።
[41] ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ጌታችን ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር።
[42] እርሱም መጀመሪያ ወንድሙ ስምዖንን አግኝቶ “በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት መሲሕን አገኘነው ” አለው።
[43] እርሱም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ወሰደው፤ ጌታችን ኢየሱስም ባየው ጊዜ ፥ “ አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህን? አንተ ኬፋ ትባላለህ፤” አለው፤ ትርጓሜውም ጴጥሮስ ማለት ነው።
[44] በማግሥቱም ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ወደደ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ ” አለው።
[45] ፊልጶስ ግን ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር።
[46] ፊልጶስም ናትናኤልን አገኘውና ፥ “ሙሴ በኦሪት፥ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው ” አለው።
[47] ናትናኤልም ፥ “በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻላልን?” አለው፤ ፊልጶስም ፥ “መጥተህ እይ ” አለው።
[48] ጌታችን ኢየሱስም ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ ባየው ጊዜ ስለ እርሱ “እነሆ፥ በልቡ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይህ ነው ” አለ።
[49] ናትናኤልም ፥ “በየት ታውቀኛለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ በበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ ” አለው።
[50] ናትናኤልም መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንተ ነህ ” አለው።
[51] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “በበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስለ አልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ ” አለው።
[52] “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማያት ሲከፈቱ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወርዱና ሲወጡ ታያላችሁ ” አላቸው።