[1] በሦስተኛውም ቀን የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ሰርግ ሆነ፤ የጌታችን የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች።
[2] ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።
[3] የወይን ጠጃቸውም ባለቀ ጊዜ እናቱ ጌታችን ኢየሱስን ፥ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም ” አለችው።
[4] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንቺ ሆይ ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም ” አላት።
[5] እናቱም ለአሳላፊዎቹ ፥ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ” አለቻቸው።
[6] በዚያም እንደ አይሁድ ልማድ የሚያነጹባቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር።
[7] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው ” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም እስከ ላይ ሞሉአቸው።
[8] “አሁንም ቅዱና ወስዳችሁ ለአሳዳሪው ስጡት ” አላቸው፤ ወስደውም ሰጡት።
[9] አሳዳሪውም ያን የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣም አላወቀም፤ የቀዱት አሳላፊዎች ግን የወይን ጠጅ የሆነውን ያን ውኃ ያውቁ ነበር። ውኃዉን የሞሉ እነርሱ ነበሩና።
[10] አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ ፥ “ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን አቈየህ ” አለው።
[11] ጌታችን ኢየሱስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራት መጀመሪያ ይህ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት።
[12] ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ፥ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ።
[13] የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
[14] በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ።
[15] የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን፥ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ።
[16] ርግብ ሻጮችንም ፥ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ ” አላቸው።
[17] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “የቤትህ ቅናት በላኝ ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ።
[18] አይሁድም መልሰው ፥ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት።
[19] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ ” ብሎ መለሰላቸው።
[20] አይሁድም ፥ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት።
[21] እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር።
[22] ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ።
[23] ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ።
[24] እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና።
[25] የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።