[1] ጌታችን ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርትን እንደ አበዛና እንደሚያጠምቅ ፈሪሳውያን መስማታቸውን ዐወቀ።
[2] ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ እርሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ አላጠመቀም።
[3] የይሁዳንም ምድር ትቶ ዳግመኛ ወደ ገሊላ ሄደ።
[4] በሰማርያ በኩልም ሲያልፍ ሳለ፥
[5] ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው በወይን ቦታ አቅራቢያ ወደ አለችው ሲካር ወደምትባለው የሰማርያ ከተማ ደረሰ።
[6] በዚያም የያዕቆብ የውኃ ጕuድጓድ ነበረ። ጌታችን ኢየሱስም መንገድ በመሄድ ደክሞ በዚያ ጕuድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር።
[7] እነሆ፥ ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ውኃ አጠጪኝ ” አላት።
[8] ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና።
[9] ያቺ የሰማርያ ሴትም ፥ “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን፥ እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ልትጠጣ ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በሥርዐት አይተባበሩም ነበርና።
[10] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው ነበር፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር ” ብሎ መለሰላት።
[11] ያቺ ሴትም እንዲህ አለችው ፥ “ጌታዬ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጕuድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?
[12] ይህን ጕuድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ አንተ ትበልጣለህን? እርሱም ልጆቹም፥ ከብቶቹም ከእርሱ ጠጥተዋል።”
[13] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት ፥ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ዳግመኛ ይጠማል።
[14] እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል እንጂ።”
[15] ሴቲቱም ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እንዳልጠማ፥ ዳግመኛም ውኃ ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ እባክህ ከዚህ ውኃ ስጠኝ፤” አለችው።
[16] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሂደሽ ባልሽን ጥሪና ወደዚህ ነይ ” አላት።
[17] ሴቲቱም ፥ “ባል የለኝም ” ብላ መለሰችለት፤ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላት ፥ “ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ።
[18] ቀድሞ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ ዛሬ አብሮሽ ያለው ግን ባልሽ አይደለም፤ ይህንስ እውነት አልሽ።”
[19] ሴቲቱም እንዲህ አለችው ፥ “ጌታዬ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ።
[20] አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ይሰግዱበት ዘንድ የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ።”
[21] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላት ፥ “አንቺ ሴት በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ብቻ ለአብ የማይሰግዱበት ሰዓት እንደምትመጣ እመኝኝ።
[22] እናንተ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ለምናውቀው እንሰግዳለን፤ መድኀኒት ከአይሁድ ወገን ነውና።
[23] ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ በመንፈስና በእውነት ለአብ የሚሰግዱባት ጊዜ ትመጣለች፤ እርስዋም አሁን ናት። አብ እንዲህ የሚሰግዱለትን ይሻልና።
[24] እግዚአብሔር መንፈስ ነውና፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ይሰግዱለት ዘንድ ይገባል።”
[25] ሴቲቱም ፥ “ክርስቶስ የሚሉት መሲሕ እንደሚመጣ እናውቃለን፤ እርሱም በሚመጣ ጊዜ ሁሉን ይነግረናል ” አለችው።
[26] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ ” አላት።
[27] በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡ፤ ከሴት ጋርም ይነጋገር ነበርና ተደነቁ፤ ነገር ግን ፥ “ምን ትሻለህ? ወይስ ከእርስዋ ጋር ለምን ትነጋገራለህ?” ያለው የለም።
[28] ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ገባች፤ ለሰዎችም ነገረች።
[29] “የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ታዩ ዘንድ ኑ፤ እንጃ፥ እርሱ ክርስቶስ ይሆን?”
[30] ከከተማም ወጥተው ወደ እርሱ ሄዱ።
[31] በዚህም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ፥ “መምህር ሆይ፥ እህል ብላ ” ብለው ለመኑት።
[32] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እኔ የምበላው እናንተ የማታውቁት ምግብ አለኝ ” አላቸው።
[33] ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው ፥ “አንዳች የሚበላው ምግብ ያመጣለት ሰው ይኖር ይሆን?” ተባባሉ።
[34] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፥ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።
[35] እናንተ እስከ አራት ወር ድረስ መከር ይሆናል የምትሉ አይደለምን? እነሆ፥ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ መከሩም ሊደርስ እንደ ገረጣ ምድሩን ተመልከቱ።
[36] አጫጅም ዋጋውን ያገኛል፤ የሚዘራና የሚያጭድም በአንድነት ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።
[37] አንዱ ይዘራል፥ ሌላውም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአል።
[38] እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ።”
[39] “የሠራሁትን ሁሉ ነገረኝ ” ብላ የመሰከረችው ሴት ስለ ነገረቻቸውም ከዚያች ከሰማርያ ከተማ ብዙዎች አመኑበት።
[40] ሳምራውያንም ሁሉ ወደ እርሱ መጥተው በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ማለዱት፤ ሁለት ቀንም ያህል በዚያ ተቀመጠ።
[41] ስለ ቃሉም እጅግ ብዙዎች አመኑበት።
[42] ሴቲቱንም ፥ “እኛ ራሳችን ይህ በእውነት የዓለም መድኀኒት ክርስቶስ እንደ ሆነ ሰምተንና ተረድተን ነው እንጂ በአንቺ ቃል ያመንበት አይደለም ” አሏት።
[43] ከሁለት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ።
[44] ነቢይ በገዛ ሀገሩ እንደማይከብር እርሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ መሰከረ።
[45] ወደ ገሊላም ደግሞ በገባ ጊዜ ገሊላውያን ሁሉ ተቀበሉት፤ እነርሱ ለበዓል ሄደው ስለ ነበር በበዓሉ ቀን በኢየሩሳሌም ያደረገውን ተአምር አይተው ነበርና።
[46] ጌታችን ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወደ አደረገበት የገሊላ ክፍል ወደምትሆን ወደ ቃና ዳግመኛ ሄደ። በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት የንጉሥ ወገን የሆነ አንድ ሰው ነበረ፤
[47] እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ሄደ፤ ሊሞት ቀርቦ ነበርና ወርዶ ልጁን ያድንለት ዘንድ ለመነው፤
[48] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ምልክትንና ድንቅ ሥራን ካላያችሁ አታምኑም ” አለው።
[49] ያም የንጉሥ ወገን የሆነ ሰው ፥ “አቤቱ፥ ልጄ ሳይሞት ፈጥነህ ውረድ ” አለው።
[50] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሂድ፤ ልጅህስ ድኖአል ” አለው፤ ያም ሰው ፥ ጌታችን ኢየሱስ በነገረው ቃል አምኖ ሄደ።
[51] ሲወርድም አገልጋዮቹ ተቀበሉትና ፥ “ልጅህስ ድኖአል ” ብለው ነገሩት።
[52] የዳነባትን ሰዓቷንም ጠየቃቸው፤ “ትናንትና በሰባት ሰዓት ንዳዱ ተወው ” አሉት።
[53] አባቱም፥ ጌታችን ኢየሱስ ፥ “ልጅህ ድኖአል ” ባለበት ሰዓት እንደ ሆነች ዐወቀ፤ እርሱም፥ ቤተ ሰቦቹም ሁሉ አመኑ።
[54] ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ተአምር ይህ ነው።