Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:05

[1] ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።

[2] እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው ፥ “መምህር ሆይ፥ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና።”

[3] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም ” አለው።

[4] ኒቆዲሞስም ፥ “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” አለው።

[5] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።

[6] ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና።

[7] ስለዚህም ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስለ አልሁህ አታድንቅ።

[8] ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳልና፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የሚወለድ ሁሉ እንዲሁ ነው።”

[9] ኒቆዲሞስም መልሶ ፥ “ይህ ሊሆን እንዴት ይቻላል?” አለው።

[10] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም?” አለው።

[11] እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም።

[12] በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ?

[13] ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው።

[14] ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው።

[15] ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ።

[16] በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና።

[17] ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና።

[18] በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና።

[19] ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና።

[20] ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም።

[21] እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና።

[22] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ።

[23] ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር።

[24] ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና።

[25] ከዚህም በኋላ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ፤

[26] ወደ ዮሐንስም ሄደው ፥ “መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ካንተ ጋር የነበረው፥ አንተም የመሰከርህለት እርሱ እነሆ፥ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይሄዳል ” አሉት።

[27] ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለ ፥ “ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ሊያደርግ ምንም አይችልም።

[28] እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን እንድሰብክለት ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልኋችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቼ ናችሁ።

[29] ሙሽራ ያለችው ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው የሙሽራው ሚዜ ግን በሙሽራው ቃል እጅግ ደስ ይለዋል፤ የእኔ ደስታ አሁን ተፈጸመች።

[30] የእርሱ ትበዛለች፤ የእኔ ግን ታንስ ዘንድ ይገባል።”

[31] ከላይ የመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የተገኘውም ምድራዊ ነው፤ የምድሩንም ይናገራል፤ ከሰማይ የመጣው ግን ከሁሉ በላይ ነው።

[32] ባየውና በሰማው ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን የሚቀበለው የለም።

[33] ምስክርነቱን የተቀበለ ግን እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።

[34] እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።

[35] አብ ልጁን ይወዳልና፥ ሁሉን በእጁ ሰጠው።

[36] በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር የቐጣ መቅሠፍት በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።

የዮሐንስ ወንጌል። — Chapters