[1] ከፋሲካ በዓል አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ወደ ላከው ወደ አብ ይሄድ ዘንድ ጊዜው እንደ ደረሰ ባወቀ ጊዜ በዓለም ያሉትን የወደዳቸውን ወገኖቹን ፈጽሞ ወደዳቸው።
[2] ራት ሲበሉም አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ሰው በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ።
[3] ጌታችን ኢየሱስም፥ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው፥ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ባወቀ ጊዜ፥
[4] ራት ከሚበሉበት ተነሥቶ ልብሱን አኖረና ማበሻ ጨርቅ አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ።
[5] በኵuስኵuስቱም ውኃ ቀድቶ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ጀመር፤ በዚያ በታጠቀው ማበሻ ጨርቅም አበሰ።
[6] ወደ ስምዖን ጴጥሮስም ደረሰ፤ እርሱም ፥ “አቤቱ፥ አንተ እግሬን ታጥበኛለህን?” አለው።
[7] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፤ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ ” ብሎ መለሰለት።
[8] ጴጥሮስም ፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት።
[9] ስምዖን ጴጥሮስም ፥ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆቼንና ራሴንም እንጂ እግሮቼን ብቻ አይደለም፤” አለው።
[10] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም ” አለው።
[11] ጌታችን ኢየሱስም አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ስለዚህ “ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም ” አለ።
[12] እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ለበሰና እንደ ገና ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን?
[13] እናንተ ‘መምህራችን፥ ጌታችንም ’ ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና።
[14] እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል።
[15] እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።
[16] እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም።
[17] ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ።
[18] ነገር ግን ይህን የምናገር ስለ ሁላችሁ አይደለም፤ የመረጥኋቸው እነማን እንደ ሆኑ እኔ አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚመገብ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።
[19] በሆነም ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ ከመሆኑ አስቀድሞ እነግራችኋለሁ።
[20] እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”
[21] ይህንም ተናግሮ ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ መሰከረ፤ እንዲህም አለ ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል።”
[22] ደቀ መዛሙርቱም ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ተጠራጥረው እርስ በርሳቸው ተያዩ፤
[23] ጌታችን ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ተቀምጦ ነበር።
[24] ስምዖን ጴጥሮስም እርሱን ጠቀሰና ፥ “ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ጠይቀህ ንገረን ” አለው።
[25] ያም ደቀ መዝሙር በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ቀረብ ብሎ ፥ “ጌታ ሆይ፥ እርሱ ማነው?” አለው።
[26] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ይህ እኔ እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የምሰጠው ነው ” አለው፤ ያን ጊዜም እንጀራ በወጥ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰጠው።
[27] እንጀራውንም ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረበት፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እንግዲህ የምታደርገውን ፈጥነህ አድርግ ” አለው።
[28] አብረውትም በማዕድ የተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው አላወቁም።
[29] ሙዳየ ምጿቱ በይሁዳ ዘንድ ነበረና፥ ለበዓል የምንሻውን ወይም ለነዳያን የምንሰጠውን ግዛ ያለው የመሰላቸው ነበሩ።
[30] ይሁዳም ያን እንጀራ ተቀብሎ ወዲያውኑ ወጣ፥ ሌሊትም ነበር።።
[31] ይሁዳም ከወጣ በኋላ ያንጊዜ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው ፥ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ከበረ።
[32] እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፥ ያንጊዜም ያከብረዋል።
[33] ልጆቼ ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር አለሁ፤ ትሹኛላችሁ፤ ለአይሁድም እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁንም ለእናንተ እነግራችኋለሁ።
[34] “እርስ በርሳችሁ ቷደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።
[35] እርስ በርሳችሁም ብቷደዱ፥ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ሁሉ ያውቌችኋል።”
[36] ስምዖን ጴጥሮስም ፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ ” አለው።
[37] ጴጥሮስም ፥ “ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ነፍሴንም እንኳ ቢሆን ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ ” አለው።
[38] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ዶሮ አይጮህም።