Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:34

[1] “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው።

[2] በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው።

[3] ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።

[4] ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ይከተሉታል፤ ቃሉን ያውቃሉና።

[5] ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፤ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።”

[6] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸውን አላወቁም።

[7] ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ።

[8] ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ነገር ግን፤ በጎች አልሰሙአቸውም።

[9] እውነተኛዉ የበጎች በር እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩልም የሚገባ ይድናል፤ ይገባልም ይወጣልም፤ መሰማርያም ያገኛል።

[10] ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም፤ እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።

[11] “ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል።

[12] ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኵuላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵuላም መጥቶ በጎችን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም።

[13] ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎችም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና።

[14] ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል።

[15] አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎቼም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ።

[16] ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ።

[17] ስለዚህም፤ አብ ይወድደኛል፥ እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና።

[18] ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፤ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤ ይህንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።”

[19] ስለዚህም ነገር አይሁድ እንደገና እርስ በርሳቸው ተለያዩ።

[20] ከእነርሱም ብዙዎች ፥ “ጋኔን ይዞት ያብዳል፤ ለምንስ ታዳምጡታላችሁ?” አሉ።

[21] ሌሎችም ይህ ነገር ጋኔን ከያዘው ሰው የሚገኝ አይደለም፤ ጋኔን የዕዉሮችን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ።

[22] በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበር።

[23] ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር።

[24] አይሁድም እርሱን ከብበው ፥ “እስከ መቼ ድረስ ሰውነታችንን ታስጨንቀናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን ” አሉት።

[25] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “አታምኑኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እኔ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ እርሱ ምስክሬ ነው።

[26] እናንተ ግን አታምኑኝም፤ እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ውስጥ አይደላችሁምና።

[27] የእኔ የሆኑ በጎቼ ግን ቃሌን ይሰሙኛል፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል።

[28] እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለሙም አይጠፉም፤ ከእጄም የሚነጥቃቸው የለም።

[29] እነርሱን የሰጠኝ አባቴ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና፤ ከአባቴም እጅ መንጠቅ የሚችል የለም።

[30] እኔና አብ አንድ ነን።”

[31] ዳግመኛም አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ።

[32] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ በየትኛው ሥራ ምክንያት ትወግሩኛላችሁ?”

[33] አይሁድም ፥ “አንተ፥ ሰው ስትሆን ራስህን እግዚአብሔርን ታደርጋለህና፤ ስለ መሳደብህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህስ አንወግርህም ” አሉት።

[34] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን?

[35] የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው፥ የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም።

[36] እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብላችሁ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለምም የላከውን እንዴት ትሳደባለህ? ትሉኛላችሁ።

[37] የአባቴን ሥራ ባልሠራ በእኔ አትመኑ።

[38] ከሠራሁ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ታውቁና ትረዱ ዘንድ ሥራዬን እመኑ።”

[39] ዳግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አመለጠ።

[40] ዳግመኛም ቀድሞ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ።

[41] ብዙዎችም ወደ እርሱ ሄደው ፥ “ዮሐንስ ምንም ያደረገው ተአምራት የለም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ሆነ ” አሉ።

[42] በዚያም ብዙ ሰዎች አመኑበት።

የዮሐንስ ወንጌል። — Chapters