[1] ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
[2] በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት።
[3] በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃዉን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር።
[4] የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያዉ ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃዉ መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና።
[5] በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር።
[6] ጌታችን ኢየሱስም ያን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቈየ ዐውቆ ፥ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው።
[7] ድውዩም መልሶ ፥ “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ ነገር ግን ውኃዉ በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ” አለው።
[8] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ” አለው።
[9] ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች።
[10] አይሁድም የዳነውን ሰው ፥ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም ” አሉት።
[11] እርሱም መልሶ ፥ “ያዳነኝ እርሱ ፥ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ” አላቸው።
[12] አይሁድም ፥ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት።
[13] ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና።
[14] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና ፥ “እነሆ፥ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ ” አለው።
[15] ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው።
[16] ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና።
[17] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ ” አላቸው።
[18] ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው ” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል ” በማለት ነው እንጂ።
[19] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል።
[20] አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል።
[21] አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል።
[22] አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ።
[23] ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም።
[24] እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም።
[25] “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ይድናሉ።
[26] ለአብ በራሱ ሕይወት እንዳለው፥ እንዲሁም ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጠው።
[27] የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው።
[28] “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ።
[29] መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ።
[30] እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና።
[31] “እኔ ለራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም።
[32] ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የመሰከረው ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።
[33] እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችሁ አልነበረምን? እርሱም ምስክርነቱን በእውነት ነገራችሁ።
[34] እኔ ግን የሰውን ምስክርነት የምሻ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ ትድኑ ዘንድ ይህን እላለሁ።
[35] እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም አንዲት ሰዓት በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።
[36] እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ ልሠራውና ልፈጽመው አባቴ የሰጠኝ ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ያ የምሠራው ሥራ ምስክሬ ነውና።
[37] የላከኝ አብም ስለ እኔ መስክሮአል፤ ከሆነም ጀምሮ ቃሉን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም።
[38] ቃሉም የላችሁም፤ በእናንተ ዘንድም አይኖርም፤ እርሱ የላከውን አላመናችሁምና።
[39] መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱ የዘለዓለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤ እነርሱም የእኔ ምስክሮች ናቸው።
[40] ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።
[41] እኔ ከሰው ክብርን ልቀበል አልሻም።
[42] ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በእናንተ እንደሌለባችሁ ዐወቅሁ።
[43] እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፥ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።
[44] ከባልንጀራችሁ ክብርን የምትመርጡ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም ክብርን የማትሹ እናንተ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?
[45] እኔ በአብ ዘንድ የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከስሳችሁስ አለ፤ እርሱም እናንተ ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።
[46] ሙሴንስ አምናችሁት ቢሆን እኔንም ባመናችሁኝ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።
[47] ሙሴ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”