Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:56

[1] “እንዳትሰናከሉ ይህን ነገርኋችሁ።

[2] ከምኵuራባቸው ያስወጡአችኋል፤ ደግሞም እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚያቀርብ የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።

[3] ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንም፥ እኔንም ስላላወቁ ነው።

[4] ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ። አስቀድሜ ግን ይህን አልነገርክኋችሁም ነበር፤ ከእናንተ ጋር ነበርሁና።

[5] አሁን ግን ወደ ላከኝ ወደ አብ እሄዳለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እንኳ ፥ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ አይጠይቀኝም።

[6] ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ በልባችሁ ኀዘን ሞላ።

[7] “እኔ በእውነት የሚሆነውን እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።

[8] እርሱም በመጣ ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአትና ስለ ጽድቅ፥ ስለ ፍርድም ይዘልፈዋል።

[9] ስለ ኀጢኣት፥ በእኔ አላመኑምና ነው፤

[10] ስለ ጽድቅ፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፥ እንግዲህ ወዲህም አታዩኝምና ነው።

[11] ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዢ ይፈረድበታልና ነው።

[12] “የምነግራችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም።

[13] ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ እርሱ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።

[14] እርሱም እኔን ያከብረኛል፤ ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋልና።

[15] ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ።

[16] “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፤ ወደ አብ እሄዳለሁና።”

[17] ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው ፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፥ ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ነገር ምንድነው?” ተባባሉ።

[18] “ይህ ጥቂት የሚለን ምንድነው? የሚናገረውን አናውቅም ” አሉ።

[19] ጌታችን ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደሚሹ ዐውቆ እንዲህ አላቸው ፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ ” ስለ አልኋችሁ፥ ስለዚህ ነገር እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን?

[20] “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

[21] ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራቷ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ልጅዋን ከወለደች በኋላ ስለ ደስታዋ ከዚያ ወዲያ ምጥዋን አታስበውም፤ በዓለም ወንድ ልጅን ወልዳለችና።

[22] እናንተም ዛሬ ታዝናላችሁ፤ እንደገናም አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

[23] ያንጊዜም እኔን የምትለምኑኝ አንዳች የለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በስሜ አብን ብትለምኑት ሁሉን ይሰጣችኋል።

[24] እስካሁን ምንም በስሜ አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም ይሆን ዘንድ ለምኑ፤ ታገኙማላችሁ።

[25] “ዛሬስ በምሳሌ ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን የአብን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ እንጂ ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል።

[26] ያንጊዜ በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምነዋለህ አልላችሁም፤

[27] እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ፤ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስለ አመናችሁብኝ እርሱ ራሱ አብ ወድዷችኋልና።

[28] ከአብ ወጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጣሁ፤ ዳግመኛም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ።”

[29] ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት ፥ “እነሆ፥ ዛሬ ገልጠህ ትናገራለህ፤ ምንም በምሳሌ የተናገርኸው የለም።

[30] አሁን አንተ ሁሉን እንደምታውቅ፥ ማንም ሊነግርህ እንደማትሻ ዐወቅን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን።”

[31] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “አሁን ታምናላችሁን?

[32] እያንዳንዳችሁ በየቦታዉ የምትበታተኑበት፥ እኔንም ብቻዬን የምትተዉበት ጊዜ ይደርሳል፤ ደርሶአልም፤ እኔ ግን ብቻዬን አይደለሁም፤ አብ ከእኔ ጋር ነውና።

[33] በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።”

የዮሐንስ ወንጌል። — Chapters