[1] ከተራራም ሲወርድ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
[2] እነሆ፥ አንድ ለምጻም ሰው መጥቶ ፥ “አቤቱ! ከወደድህስ እኔን ማንጻት ይቻልሃል ” እያለ ሰገደለት።
[3] እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ ንጻ ” አለው፤ ያንጊዜም ከለምጹ ነጻ።
[4] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሂድና ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ሊሆንባቸው ሙሴ እንደ አዘዘ መባህን አቅርብ ” አለው።
[5] ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ መጥቶ ፥
[6] “አቤቱ! ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝትWaል ” ብሎ ለመነው።
[7] ጌታችን ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ ” አለው።
[8] የመቶ አለቃውም መልሶ ፥ “አቤቱ! አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ፤ ልጄም ይድናል፤
[9] እኔም እኮ የምገዛ ሰው ነኝ፤ የማዝዛቸውም ጭፍሮች አሉኝ፤ ይህን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል ” አለው።
[10] ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ አደነቀ፤ ለሚከተሉትም እንዲህ አለ ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል ሁሉ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም፤
[11] ነገር ግን እላችኋለሁ ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማያትም ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም አጠገብ ይቀመጣሉ።
[12] የመንግሥትን ልጆች ግን በውጭ ወደ አለ ጨለማ ይጥሏቸዋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
[13] ጌታችን ኢየሱስም የመቶ አለቃውን እንዲህ አለው ፥ “እንግዲህ ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ።” ልጁም በዚያ ሰዓት ዳነ፤ መስፍኑም ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ልጁ ድኖ አገኘው።
[14] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስን አማት በንዳድ ታማ ተኝታ አገኛት።
[15] እጅዋንም ይዞ ዳሰሳት፤ ንዳዱም ተዋት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።
[16] በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ አጋንንትንም በቃሉ አወጣቸው። የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
[17] ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ ፥ “ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ ” ብሎ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።
[18] ጌታችን ኢየሱስም በዙሪያው የተሰበሰቡትን ብዙ ሰዎች በአየ ጊዜ ባሕሩን ተሻግረው እንዲሄዱ አዘዘ።
[19] አንድ ጸሓፊ ወደ እርሱ መጥቶ ፥ “መምህር፥ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህን?” አለው።
[20] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ለቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፤ ለሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም ” አለው።
[21] ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ ፥ “ጌታ ሆይ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን ልቅበር ፍቀድልኝ ” አለው።
[22] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተስ ተከተለኝ፤ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸው ” አለው።
[23] ወደ ታንኳ በወጣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
[24] እነሆም፥ የባሕሩ ማዕበል ታንኳውን እስኪደፍነው ድረስ በባሕሩ ውስጥ ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።
[25] ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና ፥ “አቤቱ! እንዳንሞት አድነን ” አሉት።
[26] እርሱም ፥ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ ምን ያስፈራችኋል?” አላቸው፤ ተነሥቶም ነፋሳትንና የባሕሩን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ።
[27] ሰዎችም ፥ “ባሕርና ነፋሳትስ እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማነው?” እያሉ ተደነቁ።
[28] ወደ ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን ሀገር በደረሰ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተቀበሉት፤ እነርሱም ማንም በዚያች መንገድ ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።
[29] ባዩት ጊዜም ፥ “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?” እያሉ ጮኹ።
[30] ከዚያም ብዙ የእሪያ መንጋዎች ከእነርሱ ርቀው ተሰማርተው ነበሩ።
[31] እነዚያ አጋንንትም ፥ “ካወጣኸንስ በእሪያዎቹ መንጋ ላይ እንድናድር ወደዚያ ስደደን ” ብለው ለመኑት፤ እርሱም “ሂዱ ” አላቸው።
[32] ወጥተውም ሄዱ፤ በእሪያዎቹም ላይ አደሩ፤ የእሪያዎችም መንጋዎች ሁሉ ከአፋፉ እየሮጡ ወደ ባሕር ውስጥ ወደቁ፤ በውኃው ውስጥም ሞቱ።
[33] እረኟችም ሸሹ፤ ወደ ከተማይቱም ገብተው ነገሩን ሁሉ፥ አጋንንትም ባደሩባቸው የሆነውን አወሩ።
[34] እነሆ፥ በከተማዋ ያሉት ሁሉ ጌታችን ኢየሱስን ሊቀበሉት ወጡ፤ ባዩት ጊዜም ከሀገራቸው እንዲሄድ ለመኑት።