Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:53

[1] በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።

[2] እንዲህ ሲል ፥ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ።

[3] የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚያስተምር የዐዋጅ ነጋሪ ቃል ” ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረለት ይህ ነውና።

[4] የዮሐንስም ልብሱ የግመል ጠጕuር ነበር፤ በወገቡም የጠፍር መታጠቂያ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር ነበር።

[5] ያን ጊዜ በይሁዳና በኢየሩሳሌም፥ በዮርዳኖስም አውራጃዎች ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር።

[6] ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ ሁሉም በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።

[7] ነገር ግን፥ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ወገን ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ብዙ ሰዎችን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቐጣ ትሸሹ ዘንድ ማን አመለከታችሁ?

[8] እንግዲህስ ለንስሓ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ።

[9] አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንዲቻለው እነግራችኋለሁ።

[10] እነሆ፥ ምሳር በዛፎች ግንድ ላይ ሊወድቅ ተቃጥቶአልና፥ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።

[11] “እኔ ለንስሓ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን ለመሸከም የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእሳትም ያጠምቃችኋል።

[12] ዐውድማውን የሚያጠራበት መንሽ በእጁ ነው፤ ስንዴውንም በጎተራ ይሰበስባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥላል።”

[13] ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።

[14] ዮሐንስ ግን “እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?” ብሎ አይሆንም አለው።

[15] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “አሁንስ ተው፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና ” አለው፤ ከዚህም በኋላ ተወው።

[16] ጌታችን ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ፥ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆ፥ ሰማይም ተከፈተለት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ።

[17] እነሆም፥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters