[1] የዳዊት ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤
[2] አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ።
[3] ይሁዳም ከትእማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤ ኤስሮምም አራምን ወለደ።
[4] አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ።
[5] ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ።
[6] እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ።
[7] ንጉሥ ዳዊትም ከኦርዮ ሚስት ሰሎሞንን ወለደ፤ ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አብያን ወለደ፤ አብያም አሳፍን ወለደ።
[8] አሳፍም ኢዮሳፍጥን ወለደ፤ ኢዮሳፍጥም ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራምም ዖዝያንን ወለደ።
[9] ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታምም አካዝን ወለደ፤ አካዝም ሕዝቅያስን ወለደ።
[10] ሕዝቅያስም ምናሴን ወለደ፤ ምናሴም አሞጽን ወለደ፤ አሞጽም ኢዮስያስን ወለደ።
[11] ኢዮስያስም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ።
[12] ከባቢሎን ምርኮም በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ።
[13] ዘሩባቤልም አብዩድን ወለደ፤ አብዩድም ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዛርን ወለደ።
[14] አዛርም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ።
[15] ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማትያንን ወለደ፤ ማትያንም ያዕቆብን ወለደ።
[16] ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለ ጌታ ኢየሱስ ከእርስዋ የተወለደ የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።
[17] እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው። ትውልድም ሁሉ ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ዐርባ ሁለት ትውልድ ነው።
[18] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።
[19] እጮኛዋ ዮሴፍ ግን ጻድቅ ነበረና ሊገልጣት አልወደደም፤ በስውርም ሊተዋት አሰበ።
[20] እርሱ ግን ይህን ሲያስብ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህ ሲል ፥ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።
[21] ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።”
[22] ይህም ሁሉ የሆነ ከእግዚአብሔር ዘንድ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፤ እንዲህ ሲል ፥
[23] “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው።”
[24] ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውን ማርያምንም ወሰዳት።
[25] የበኽር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።