[1] ከስድስት ቀንም በኋላ፥ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸው ወደ ረዥም ተራራ አወጣቸው።
[2] መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።
[3] እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።
[4] ጴጥሮስም መልሶ ጌታችን ኢየሱስን ፥ “አቤቱ፥ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ ” አለው።
[5] እርሱም ገና ይህን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ እነሆ፥ ከደመናው ውስጥም “የምወደው፥ በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት ” የሚል ቃል መጣ።
[6] ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በግንባራቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር።
[7] ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው፤ “ተነሡ፥ አትፍሩም ” አላቸው።
[8] ዐይናቸውንም አቅንተው አዩ፤ ነገር ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ብቻ በቀር ያዩት ማንም አልነበረም።
[9] ከተራራውም ሲወርዱ ጌታችን ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን ተለይቶ እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ ” ብሎ አዘዛቸው።
[10] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት።
[11] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ አዎን፥ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፥ ሁሉንም ያቀናል።
[12] ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ፈጽሞ መጥትWaል፤ የወደዱትንም ሁሉ በእርሱ ላይ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁ የሰው ልጅም ከእነርሱ መከራን ይቀበል ዘንድ አለው።”
[13] ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው ዐወቁ።
[14] ወደ ሕዝቡም በደረሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እየለመነ ሰገደለት።
[15] እንዲህም አለ ፥ “አቤቱ፥ ልጄን ማርልኝ፤ ክፉ ጋኔን በየወሩ መጀመሪያ ያሠቃየዋልና፥ ይዞ ይጥለዋልና፤ ብዙ ጊዜም ወደ እሳት ይጥለዋል፤ ወደ ውኃም የሚጥልበት ጊዜ አለ።
[16] ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት፤ እርሱንም ማዳን ተሳናቸው።”
[17] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ ፥ “የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ድረስ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ አምጡልኝ ” አለ።
[18] ጌታችን ኢየሱስም ገሠጸውና ጋኔኑ ከእርሱ ወጣ፤ በዚያች ሰዓትም ልጁ ዳነ።
[19] ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ቀርበው ጌታችን ኢየሱስን ፥ “ስለምን እኛ ማውጣት ተሳነን?” አሉት።
[20] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ስለ እምነታችሁ መጒደል ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ ተነቅለህ ሂድ ብትሉት ይፈልሳል፤ የሚሳናችሁ ነገርም የለም።
[21] ይህ ዓይነት ግን ያለ ጿምና ጸሎት አይወጣም ” አላቸው።
[22] በገሊላም ሲመላለሱ፥ ጌታችን ኢየሱስ ፥ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤
[23] ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሰምተው እጅግ አዘኑ።
[24] ወደ ቅፍርናሆምም በደረሱ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተው ፥ “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር አይገብርምን?” አሉት።
[25] እርሱም ፥ “አዎን ” አለ፤ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ አስቀድሞ ፥ “ስምዖን ሆይ፥ ምን ትላለህ? የምድር ነገሥታት ቀረጥንና ግብርን ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?” አለው።
[26] ጴጥሮስም “ከሌሎች ነው ” አለ፤ ጌታችን ኢየሱስም አለው፤ “እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው።
[27] ነገር ግን፤ እንዳያጒረመርሙ ወደ ባሕር ሂድና መረብ ጣል፤ በመጀመሪያ የያዝኸውን ዓሣ ወስደህ አፉን ክፈት፤ በውስጡም ሰጣጢራ ታገኛለህ፤ ይኸውም አራት ድሪም ነው፤ እርሱንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው ” አለው።