[1] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው።
[2] “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል።
[3] ስለዚህ ያስተማሩአችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እንደሚሠሩት አታድርጉ፤ የሚያስተምሩትን አይሠሩትምና።
[4] ትልቅና ከባድ ሸክም አስረው ሰውን በጫንቃው ላይ ያሸክሙታል፤ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።
[5] የሚሠሩትን ሥራቸውን ሁሉ ለሰው ሊታዩ ይሠሩታልና፤ አሸንክታባቸውን ይዘረጋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ።
[6] በማዕድ ጊዜ በክብር ስፍራ፥ በምኵuራብም በፊተኛው ወንበር መቀመጥን ይወድዳሉ።
[7] በገበያም ሰዎች እጅ እንዲነሱአቸውና መምህር ሆይ፥ እንዲሉአቸው ይወድዳሉ።
[8] እናንተስ መምህራን ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ነውና፤ እናንተስ ሁላችሁ ወንድማማቾች ናችሁ።
[9] የሰማዩ አባታችሁ አንድ ነውና በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ።
[10] ሊቃችሁ አንድ፤ እርሱም ክርስቶስ ነውና በምድር ላይ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ፤
[11] ነገር ግን ከእናንተ የሚበልጠው አገልጋይ ይሁናችሁ።
[12] ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ይከብራልና።
[13] “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ጸሎታችሁን በማብዛት ምክንያት የመበለቶችን ገንዘብ ስለምትበሉ ወዮላችሁ! ስለዚህ ጽኑ ፍርድን ትቀበላላችሁ።
[14] እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም አትገቡም፤ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክሉአቸዋላችሁ።
[15] እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድን ሰው ለማሳመን ባሕሩንና የብሱን ስለምትዞሩ ወዮላችሁ! ካመነም በኋላ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ።
[16] በቤተ መቅደስ የሚምል ኀጢአት የለበትም፤ በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን ይበድላል የምትሉ ዕውራን መሪዎች እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ!
[17] እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ የትኛው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የሚቀድሰው ቤተ መቅደስ?
[18] ደግማችሁም በመሠዊያው የሚምል አይበድልም፤ በላዩ በአለው በመሥዋዕቱ የሚምል ግን ይበድላል ትላላችሁ።
[19] እናንተ ሰነፎችና ዕውራን፥ የትኛው ይበልጣል? መሥዋዕቱ ነውን? ወይንስ መሥዋዕቱን የሚቀድሰው መሠዊያው?
[20] በመሠዊያው የሚምል በእርሱ ይምላል፤ በእርሱ ላይም ባለው ሁሉ ይምላል።
[21] በቤተ መቅደስም የሚምል በእርሱና በውስጡ በሚኖረው ሁሉ ይምላል።
[22] በሰማይ የሚምልም በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
[23] “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል፥ ከከሙንም ዐሥራትን ስለምታወጡ፥ በኦሪት ያለውንም ታላቁን ትእዛዝ፥ ፍርድንና ምጿትን፥ ታማኝነትንም ስለምትተዉ ወዮላችሁ! ይህን ልታደርጉ፥ ያንንም ላትተዉ ይገባ ነበር።
[24] እናንተ ዕውራን መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ፥ ግመልንም የምትውጡ፤
[25] “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያንና ስስትን ተሞልቶ ሳለ የጿውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጥቡ ወዮላችሁ!
[26] አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ንጹሕ ይሆን ዘንድ አስቀድመህ የጿውንና የወጭቱን ውስጡን እጠበው።
[27] በውጫቸው አምረው የሚታዩ፥ በውስጣቸው ግን የሙታን አጥንትንና ርኵuሰትን ሁሉ የተመሉ፥ የተለሰኑ መቃብሮችን የምትመስሉ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ!
[28] እንዲሁ እናንተም በውጭ ለሰው ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ዐመጽንና ግብዝነትን፥ ቅሚያንም የተሞላችሁ ናችሁ።
[29] “የነቢያትን መቃብር የምትሠሩ፥ የጻድቃንንም መቃብር የምታስጌጡ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ!
[30] በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን በነቢያት ደም ከእነርሱ ጋር ባልተባበርንም ነበር ትላላችሁ።
[31] እነሆ፥ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደ ሆናችሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ።
[32] እናንተም የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።
[33] እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ ልታመልጡ እንዴት ትችላላችሁ?
[34] ስለዚህ እነሆ፥ እኔ ነቢያትንና ጠቢባንን፥ ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ፤ ትሰቅላላችሁም፤ ከእነርሱም በምኵuራባችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዱአቸዋላችሁ።
[35] ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቃን ሁሉ ደም በእናንተ ላይ ይደርስ ዘንድ።
[36] እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚች ትውልድ ይደርስባታል።
[37] “ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል፥ ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትደበድብ፥ ዶሮ ጫጭቶችዋን በክንፎችዋ ውስጥ እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ምን ያህል ወደድሁ! እናንተ ግን እንቢ አላችሁ።
[38] እነሆ ቤታችሁ ምድረ በዳ ሆኖ ይቀርላችኋል።
[39] እውነት እላችኋለሁ፤ ‘በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው ’ እስከምትሉበት ጊዜ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ አታዩኝም።”