Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:50

[1] ጌታችን ኢየሱስ ዳግመኛ መልሶ በምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አለ ፥

[2] “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች።

[3] ለሰርጉም የታደሙትን ይጠሩአቸው ዘንድ አገልጋዮቹን ላከ፤ ሊመጡም አልወደዱም።

[4] ዳግመኛም ሌሎችን አገልጋዮች እንዲህ ብሎ ላከ፤ የታደሙትን እንዲህ በሉአቸው ፥ እነሆ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ኮርማዎቼና የሰቡ ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል። ወደ ሰርጉ ኑ።

[5] እነርሱ ግን ቸል ብለው ሄዱ፤ ወደ እርሻው የሄደ አለ፤ ወደ ንግዱም የሄደ አለ።

[6] የቀሩትም አገልጋዮቹን ይዘው ሰደቡአቸው፤ ገደሉአቸውም፤

[7] ንጉሡም ተቈጣ፤ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።

[8] ከዚህም በኋላ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ሰርጌስ ተዘጋጅቶአል፤ ነገር ግን ለአደምናቸው አልተገባቸውም።

[9] እንግዲህ ወደ ሜዳዎችና ወደ አደባባይም ሂዱና ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ።

[10] እነዚያ አገልጋዮችም ወደ መንገዶች ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም፥ በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉም ቤት በተጋባዦች ሞላ።

[11] ንጉሡም ተጋባዦቹን ሊያይ በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አገኘ።

[12] ወዳጄ ሆይ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው፤ ያም ሰው ምላሽ አጣ።

[13] ከዚህም በኋላ ንጉሡ አገልጋዮቹን፥ እጁንና እግሩን አስረው በውጭ ወደ አለ ጨለማ ይጥሉት ዘንድ አዘዘ፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

[14] የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

[15] ከዚህም በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱ፤ በአነጋገሩም ያጠምዱት ዘንድ ተማከሩ።

[16] ደቀ መዛሙርቶቻቸውንም ከሄሮድስ ቤተ ሰቦች ጋር ወደ እርሱ ላኩ፤ እነርሱም እንዲህ አሉት ፥ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ማንንም አትፈራም፤ የሰውንም ፊት አይተህ አታደላም።

[17] እንግዲህ የሚገባውን ንገረን፤ ምን ትላለህ? ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባልን? ወይስ አይገባም?” አሉት።

[18] ጌታችን ኢየሱስም ክፋታቸውን ዐወቀባቸውና ፥ “እናንት ግብዞች ለምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ገንዘብ አሳዩኝ ” አላቸው።

[19] ገንዘቡንም አመጡለት።

[20] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ይህ መልኩ፥ ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።

[21] እነርሱም “የቄሣር ነው ” አሉት፤ እርሱም “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ ” አላቸው።

[22] ይህንም ሰምተው አደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።

[23] በዚያችም ቀን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጡ።

[24] እንዲህም ብለው ጠየቁት ፥ “መምህር ሆይ፥ ሙሴ ልጅ ሳይወልድ የሞተ ሰው ቢኖር ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካለት ብሎአል።

[25] እንግዲህ ሰባት ወንድማማቾች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ታላቁም ሚስት አገባና ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ለወንድሙም ሚስቱን ተወ።

[26] እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው፥ ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።

[27] ከሁሉም በኋላ ያቺ ሴት ሞተች።

[28] እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ከሰባቱ ለማንኛው ሚስት ትሆናለች? ሁሉም አግብተዋት ነበርና።”

[29] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለ ማወቅ ትስታላችሁ።

[30] ሙታንስ በሚነሡበት ጊዜ በሰማያት እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆነው ይኖራሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም።

[31] ስለ ሙታን መነሣት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ እንዲህ ተብሎ የተነገረውን አላነበባችሁምን?

[32] እኔ እግዚአብሔር የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንግዲህ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”

[33] ሕዝቡም ሰምተው ትምህርቱን አደነቁ።

[34] ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ምላሽ እንዳሳጣቸው በሰሙ ጊዜ በአንድነት ወደ እሱ ተሰበሰቡ።

[35] ከመካከላቸውም አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ጠየቀው።

[36] “መምህር ሆይ፥ ከኦሪት ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች?” አለው።

[37] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደደው።

[38] ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

[39] የምትመስላት ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትለው ናት።

[40] ኦሪትና ነቢያት ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸንተዋል።”

[41] ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው ፥

[42] “ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” እነርሱም ፥ “የዳዊት ልጅ ነው ” አሉት።

[43] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እንግዲያ እርሱ ራሱ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንዲህ አለ?

[44] ‘ጌታ ጌታዬን ፥ ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስከ አደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።’

[45] እርሱ ራሱ ዳዊት ‘ጌታዬ ’ ያለው፥ እንግዲህ እንዴት ልጁ ይሆነዋል?”

[46] አንድም ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ የለም፤ ከዚያች ቀንም ጀምሮ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters