Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:39

[1] ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት።

[2] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም።”

[3] በደብረ ዘይትም ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት ፥ “ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድን ነው?”

[4] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤

[5] ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ።

[6] ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው።

[7] ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፥ ቸነፈርም፥ የምድር መናወጥም ይሆናል።

[8] እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

[9] ያንጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።

[10] ያንጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ።

[11] ብዙዎች ሐሰተኟች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።

[12] ከዐመፅም ብዛት የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች።

[13] እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል።

[14] በአሕዛብ ሁሉ ላይ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ያንጊዜም ፍጻሜ ይደርሳል።

[15] “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የመፍረሱን የርኵuሰት ምልክት በተቀደሰ ቦታ ቆሞ ባያችሁት ጊዜ አንባቢው ያስተውል።

[16] ያንጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።

[17] በሰገነት ያለም በቤት ውስጥ ያለውን ያነሣ ዘንድ አይውረድ።

[18] በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።

[19] ነገር ግን በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!

[20] ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ።

[21] ያንጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ያልተደረገ፥ ከእንግዲህም ወዲያ የማይደረግ ታላቅ መከራ ይሆናል።

[22] እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።

[23] ያንጊዜ እነሆ፥ ክርስቶስ በዚህ አለ፤ ወይም በዚያ አለ የሚላችሁ ሰው ቢኖር አትመኑ።

[24] ሐሰተኟች መሢሖችና ሐሰተኟች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራሉ።

[25] እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።

[26] እነሆ፥ በምድረ በዳ አለ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ እነሆም፥ በቤት ውስጥ ነው ቢሉአችሁ አትመኑ።

[27] መብረቅ ከምሥራቅ እንደሚወጣ፥ እስከ ምዕራብም እንደሚታይ የሰው ልጅም መምጣት እንዲሁ ይሆናል።

[28] ገደላ ባለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ።

[29] “ከእነዚያም ቀኖች መከራ በኋላ፥ ወዲያውኑ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይልም ይናወጣል።

[30] በዚያም ወራት የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ ያንጊዜም የምድር አሕዛብ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅንም በኀይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።

[31] መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ የተመረጡትንም ከሰማይ ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ መዐዝን ይሰበስቧቸዋል።

[32] “ምሳሌውንም ከበለስ ዕወቁ፤ ጫፍዋ የለሰለሰ፥ ቅጠልዋም የለመለመ እንደሆነ እነሆ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ።

[33] እንዲሁ እናንተ ይህን ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ እንደ ቀረበና በዳጃፍ እንዳለ ዕወቁ።

[34] እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪደረግ ድረስ ይቺ ትውልድ አታልፍም።

[35] ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።

[36] “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን የሚያውቃት የለም።

[37] በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ይሆናል።

[38] ያንጊዜ ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፥

[39] የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከ አጠፋበት ጊዜ ድረስ እንደ አላወቁ፤ የሰው ልጅም አመጣጡ እንዲሁ ይሆናል።

[40] ያንጊዜ ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።

[41] ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ ሁለተኛይቱንም ይተዋሉ፤ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።

[42] እንግዲህ ትጉ፤ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና።

[43] “ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት ቢያውቅ ተግቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቈፈር ባልተወ ነበር።

[44] ስለዚህ እናንተም ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

[45] “እንግዲህ ምግባቸውን በየጊዜዉ ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልህ አገልጋይ ማንነው?

[46] ጌታዉ በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ ብፁዕ ነው።

[47] እውነት እላችኋለሁ፤ በገንዘቡ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።

[48] ነገር ግን ያ ክፉ አገልጋይ ፥ ‘ጌታዬ ከመምጣት ይዘገያል ’ ብሎ በልቡ ቢያስብ፥

[49] ባልንጀሮቹን አገልጋዮች ቢደበድብ፥ ከሰካሮች ጋርም ቢበላና ቢጠጣ፥

[50] የዚያ አገልጋይ ጌታዉ ባልጠረጠው ዕለትና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል።

[51] ከመካከሉም ይሰነጥቀዋል፤ ዕድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters