[1] ከዚህም በኋላ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ ወሰደው።
[2] አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ጿመ፤ ከዚህም በኋላ ተራበ።
[3] የሚፈታተነውም ቀርቦ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ ” አለው።
[4] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፎአል፤” አለው።
[5] ከዚህም በኋላ፥ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመው።
[6] “አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ከዚህ መር ብለህ ወደ ታች ውረድ፤ ይጠብቁህ ዘንድ ስለ አንተ መላእክቱን ያዝዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና ” አለው።
[7] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል ” አለው።
[8] ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ እጅግ ረዥም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለሙን ሁሉ መንግሥታት፥ ክብራቸውንም ሁሉ አሳየው።
[9] “ብትሰግድልኝ፥ እጅ ብትነሳኝም ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ ” አለው።
[10] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ፥ “አንተ ሰይጣን ከአጠገቤ ሂድ፤ ለጌታህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል ” አለው።
[11] ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ተወው፤ እነሆም፥ መላእክት ሊያገለግሉት መጡ።
[12] ጌታችን ኢየሱስም ዮሐንስ እንደ ተያዘ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ።
[13] ናዝሬትንም ትቶ መጣና በዛብሎንና በንፍታሌም አገሮች መካከል በምትገኝ በባሕር አጠገብ ባለች በቅፍርናሆም ኖረ።
[14] በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ እንዲህ ሲል ፥
[15] “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ የዮርዳኖስ ማዶ አሕዛብ የሚኖሩበት ገሊላ።
[16] በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃንን አየ፤ በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩም ብርሃን ወጣላቸው።”
[17] ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ “መንግሥተ ስማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ ” እያለ ይሰብክ ጀመረ።
[18] በገሊላ ባሕር ዳር ሲመላለስም፥ ሁለቱን ወንድማማቾች ጴጥሮስ የተባለ ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና።
[19] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰውን የምታጠምዱ እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ ” አላቸው።
[20] ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
[21] ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋራ በታንኳ ውስጥ ሆነው መረባቸውን ሲያበጁ አየና ጠራቸው።
[22] እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳቸውንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
[23] ጌታችን ኢየሱስም በምኵuራባቸው እያስተማረ፥ የመንግሥቱንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይመላለስ ነበር።
[24] ዝናውም በመላው ሶርያ ተዳረሰ፤ የታመሙትን ሁሉ፥ የተጨነቁትንም፥ ደዌያቸውም ልዩ ልዩ የሆነውን፥ አጋንንትም ያደሩባቸውን፥ ጨረቃ እያየ የሚጥላቸውን፥ ልምሾዎችንም ሁሉ አመጡለት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው።
[25] ብዙ ሕዝብም ከገሊላና ዐሥር ከተማ ከሚባል አገር፥ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ተከተሉት።