Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 9:54

[1] በነጋም ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ሁሉ ጌታችን ኢየሱስን ሊገድሉት ተማከሩ።

[2] አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢው ለጰንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።

[3] ከዚህም በኋላ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ፈረዱበት ባየ ጊዜ “ንጹሕ ደምን አሳልፌ የሰጠሁ እኔ በድያለሁ ” ብሎ ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች ሠላሳውን ብር መለሰ።

[4] እነርሱ ግን ፥ “እኛ ምን አግዶን አንተ ለራስህ ዕወቅ ” አሉት።

[5] ያንም ብር በቤተ መቅደስ በትኖ ሄደና ታነቀ።

[6] የካህናት አለቆችም ያን ብር አንሥተው “የደም ዋጋ ነውና በመባ ውስጥ ልንጨምረው አይገባንም ” አሉ።

[7] ተማክረውም ለእንግዳ መቃብር የሸክላ ሠሪ መሬት ገዙበት።

[8] ስለዚህም ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት ” ተብሎ ተጠራ።

[9] ያንጊዜ የነቢዩ የኤርምያስ ቃል “የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክቡርን ዋጋ ሠላሳውን ብር ወሰዱ፤

[10] እግዚአብሔር እንደ አዘዘኝም ለሸክላ ሠሪ እርሻ ሰጡት ” ያለው ተፈጸመ።

[11] ጌታችን ኢየሱስም በመስፍኑ ፊት ቆመ፤ መስፍኑም ፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተ አልህ ” አለው።

[12] የካህናት አለቆችና የሕዝቡም ሽማግሌዎች ሲከስሱት ምንም የሰጠው መልስ የለም።

[13] ከዚህም በኋላ፤ ጲላጦስ ፥ “ይህን ያህል ሲመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው።

[14] መስፍኑ እጅግ እስኪያደንቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።

[15] በዚያም በዓል ለሕዝቡ ከእስረኟች መካከል አንዱን የወደዱትን እንዲፈታላቸው ለመስፍኑ ልማድ ነበረው።

[16] ያንጊዜም በጣም የታወቀ ስሙ በርባን የሚባል አንድ እስረኛ ነበር።

[17] እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ ሕዝቡን ፥ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን? ወይስ ክርስቶስ የሚሉት ኢየሱስን?” አላቸው።

[18] በቅንዐት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።

[19] ጲላጦስም በአደባባይ ተቀምጦ ሳለ፥ “በዚህ ጻድቅ ሰው ላይ እንዳትበድል ዕወቅ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት በሕልሜ ስለ እርሱ ብዙ ተሠቃይቻለሁና ” ስትል ሚስቱ ላከችበት።

[20] የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ግን በርባንን እንዲፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን እንዲገድሉ ሕዝቡን አባብለው እሺ አሰኙአቸው፤

[21] መስፍኑም መልሶ ፥ “ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “በርባንን ” አሉ።

[22] ጲላጦስም ፥ “እንግዲህ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም ፥ “ስቀለው!” አሉ።

[23] መስፍኑም ፥ “ምን ክፉ ሥራ ሠራ?” አላቸው፤ እነርሱ ግን “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጩኽት አበዙ።

[24] ከዚህም በኋላ ጲላጦስ ሁከት ከሚበዛ በቀር የሚጠቅም ነገር እንደሌለ ባየ ጊዜ፥ ውኃ ወስዶ ፥ “እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ለራሳችሁ ዕወቁ ” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ።

[25] ሕዝቡም ሁሉ መልሰው ፥ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን ” አሉ።

[26] ከዚህም በኋላ በርባንን ፈታላቸው፤ ጌታችን ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቅሉት ሰጣቸው።

[27] ከዚህም በኋላ የመስፍኑ ጭፍሮች ጌታችን ኢየሱስን ተቀብለው ወደ ፍርድ ሸንጎ ወሰዱት፤ ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰቡ።

[28] ልብሱንም ገፍፈው ቀይ ልብስ አለበሱት።

[29] የእሾህም አክሊል ጐንጕuነው በራሱ ላይ አቀዳጁት፤ በቀኝ እጁም ዘንግ አሲያዙት፤ በፊቱም ተንበርክከው ፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ” እያሉ ተዘባበቱበት፤

[30] በላዩም ተፉበት፤ ዘንጉንም ነጥቀው ራሱን መቱት።

[31] ከተዘባበቱበትም በኋላ፥ ቀዩን ልብስ ገፍፈው ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

[32] ሲወጡም ስምዖን የሚባል የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።

[33] ትርጓሜው የራስ ቅል ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባል ቦታ በደረሱ ጊዜ፥

[34] ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ ወይንን ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።

[35] በሰቀሉትም ጊዜ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤ ይህም “ልብሶቼን ለራሳቸው ተካፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

[36] በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር።

[37] በራሱ ላይም “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው ” የሚል የክሱን ጽሕፈት ጽፈው አኖሩ።

[38] ያንጊዜም ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ከእርሱ ጋር ሰቀሉ።

[39] የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር።

[40] “ቤተ መቅደስን የምታፈርሰው፥ በሦስተኛውም ቀን የምትሠራው አንተ ሆይ፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ እስኪ ከመስቀልህ ውረድ ” ይሉት ነበር።

[41] እንዲሁም የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ይዘብቱበት ነበር፤

[42] “ሌላውን ያድናል፤ ራሱን ማዳን ግን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድና እንመንበት።

[43] በእግዚአብሔርም ታምኗል፤ ይወደውም እንደ ሆነ እነሆ፥ አሁን ያድነው፤ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሏልና።”

[44] ከእርሱ ጋር የተሰቀሉ ወንበዴዎችም እንዲሁ ያሽሙአጥጡት ነበር።

[45] ከስድስት ሰዓት ጀምሮም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ።

[46] በዘጠኝ ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ ፥ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ፤ ይኸውም ፥ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

[47] በዚያም ቆመው የነበሩት በሰሙ ጊዜ፥ “ይህስ ኤልያስን ይጠራል ” አሉ።

[48] ያንጊዜም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወሰደ፤ ሆምጣጤም ሞላበት፤ በዘንግም አስሮ አጠጣው።

[49] “ተዉ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ ” የሚሉም ነበሩ።

[50] ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ያንጊዜም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች።

[51] እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተነዋወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ።

[52] መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩ ከቅዱሳን በድኖችም ብዙዎች ተነሡ።

[53] ከመቃብራቸውም ወጡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩአቸው።

[54] የመቶ አለቃውና ከእርሱ ጋር ጌታችን ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት ግን፤ ንውጽውጽታውንና የሆነውን ሁሉ አይተው እጅግ ፈሩ፤ “በእውነትም ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ” አሉ።

[55] የሆነውንም ሁሉ ከሩቁ የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች በዚያ ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስን የተከተሉትና ያገለገሉት ነበሩ።

[56] ከእነርሱም ማርያም መግደላዊት፥ የያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም፥ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

[57] በመሸም ጊዜ ስሙ ዮሴፍ የሚባል ባለጸጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር።

[58] እርሱም ወደ ጲላጦስ ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ለመነ፤ ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ።

[59] ዮሴፍም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ተቀብሎ በንጹሕ በፍታ ገነዘው።

[60] ለራሱ ከዐለት በአስፈለፈለው በሐዲስ መቃብርም ቀበረው፤ ታላቅ ድንጋይም አንከባሎ የመቃብሩን አፍ ገጥሞ ሄደ።

[61] ከዚያም ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር።

[62] ከዐርብም በኋላ በማግሥቱ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡ።

[63] እነርሱም እንዲህ አሉት ፥ “ጌታ ሆይ፥ ያ መስሐቲ በሕይወቱ ሳለ፥ ‘በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ’ ያለውን አሰብን። ሉቃ.

[64] እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ እንዳይሉ፥ እስከ ሦስት ቀን መቃብሩ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ የኋለኛዪቱ በደሉ ከፊተኛዪቱ የምትከፋ ትሆናለችና።”

[65] ጲላጦስም ፥ “ጠባቆች አሏችሁ፤ ሄዳችሁም እንደምታውቁ አስጠብቁ ” አላቸው።

[66] እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters