Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:25

[1] በዚያም ወራት ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት በእርሻ መካከል ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ነበርና እሸት እየቈረጡ ይበሉ ጀመር።

[2] ፈሪሳውያንም አይተው ፥ “እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ሲያደርጉ እይ ” አሉት።

[3] እርሱም አላቸው ፥ “እርሱ በተራበ ጊዜ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን፥

[4] ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ ከካህናትም ብቻ በቀር እርሱ ሊበላው የማይገባውን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሊበሉት የማይገባቸውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?

[5] በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚሽሩአት፥ በደልም እንደማይሆንባቸው በኦሪት ያለውን አላነበባችሁምን?

[6] እኔም ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ እንዳለ እላችኋለሁ።

[7] ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ ያለው ምን እንደ ሆነ ብታውቁስ ኖሮ ያልበደሉትን ባልፈረዳችሁባቸው ነበር።

[8] የሰንበት ጌታዋ የሰው ልጅ ነውና።”

[9] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ ዐልፎ ወደ ምኵuራባቸው ገባ።

[10] እነሆ፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ ይከሱት ዘንድ ፥ “በሰንበት መፈወስ ይገባልን?” ብለው ጠየቁት።

[11] እርሱም አላቸው ፥ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበትም ወደ ጕuድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ይዞ የማያወጣው ማነው?

[12] እንግዲያማ ከበግ ይልቅ ሰው እንደ ምን አይበልጥም! እንኪያስ በሰንበት መልካም ማድረግ ይገባል።”

[13] ከዚያም በኋላ ያን ሰው “እጅህን ዘርጋ ” አለው፤ እጁንም ዘረጋት፤ ያንጊዜም ድና እንደ ሁለተኛዋ ሆነች።

[14] ፈሪሳውያንም ወጥተው ሊገድሉት ስለ እርሱ ተማከሩ።

[15] ጌታችን ኢየሱስም ባወቀ ጊዜ ከዚያ ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሁሉንም አዳናቸው።

[16] እንዳይገልጡትም አዘዛቸው።

[17] በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ እንዲህ ሲል።

[18] “እነሆ፥ የመረጥሁት ልጄ፥ ነፍሴ የወደደችው፥ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱ ለአሕዛብ ፍርድን ይናገራል፤

[19] አይከራከርም፤ አይጮኽም፤ በአደባባይም ቃሉን የሚሰማ የለም።

[20] ያሸናፊነቱን ፍርድ እስኪያመጣ ድረስ የተቀጠቀጠ መቃን አይሰብርም፤ የሚጤስ የጧፍ ኩስታሪንም አያጠፋም።

[21] አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

[22] ከዚህ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ደንቆሮ አመጡለት፤ ያም ዕውር፥ ደንቆሮ እስኪናገር፥ እስኪያይም ድረስ ፈወሰው።

[23] ሕዝቡም ሁሉ እየተደነቁ፥ “ይህ የዳዊት ልጅ አይደለምን?” አሉ።

[24] ፈሪሳውያን ግን በሰሙ ጊዜ “በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል ነው እንጂ ይህስ አጋንንትን አያወጣም ” አሉ።

[25] ጌታችን ኢየሱስም ዐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው ፥ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ ከተማም ሁላ፥ ቤትም እርስ በርስዋ የምትለያይ ከሆነች አትጸናም።

[26] ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣው ከሆነ እርስ በርሱ ተለያየ፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትጸናለች?

[27] እኔስ፥ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ ልጆቻችሁ በምን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።

[28] እኔ በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ ግን፥ እንግዲያስ የእግዚአብሔር መንግሥት አሁን ወደ እናንተ ደርሳለች።

[29] ኀይለኛን አስቀድሞ ካላሰረ በስተቀር ወደ ኀይለኛ ቤት ለመግባት፥ ገንዘቡንም ለመበርበር የሚችል ማንም የለም፤ ከዚህም በኋላ ቤቱን ይበረብራል።

[30] ከእኔ ጋር ያልሆነ ባለጋራዬ ነው፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል።

[31] ስለዚህ እላችኋለሁ ፥ ለሰው ኀጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረያል፤ መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ ግን አይሰረይለትም።

[32] በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገር ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን፥ በሚመጣውም ዓለም ቢሆን አይሰረይለትም።

[33] “ወይም ዛፉን መልካም፥ ፍሬውንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፉን ክፉ፥ ፍሬውንም ክፉ አድርጉ፤ ዛፍ በፍሬው ይታወቃልና።

[34] የእባብ ልጆች ሆይ፥ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም መናገርን እንዴት ትችላላችሁ? ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራልና።

[35] ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰው ግን ከክፉ ልቡ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።

[36] እኔ ግን እላችኋለሁ ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን ስለ እርሱ መልስ ይሰጡበታል።

[37] ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገርህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።”

[38] ያንጊዜም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ወገን ሰዎች መጥተው ፥ “መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት ልናይ እንወዳለን ” አሉት።

[39] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ዐመፀኛዪቱና፤ አመንዝራዪቱ ትውልድ ምልክትን ትሻለች፤ ምልክት ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር አይሰጣትም።

[40] ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ይኖራልና።

[41] የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይህችን ትውልድ ይፋረዱአታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ።

[42] ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ተነሥታ ከዚች ትውልድ ጋር ትፋረዳለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ትሰማ ዘንድ ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ።

[43] “ርኩስ መንፈስም ከሰው ከወጣ በኋላ፥ ዕረፍት ሲሻ ውኃ ወደሌለበት ምድረ በዳ ይዞራል፤ አያገኝምም።

[44] ከዚህም በኋላ፥ እንግዲህስ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ በመጣም ጊዜ ባዶ ሆኖ፥ ተጠርጎና ተለስኖ ያገኘዋል።

[45] ከዚህም በኋላ ይሄዳል፤ ከእርሱም የሚከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንትን ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው የኋላ ኑሮው ከፊተኛው የከፋ ይሆናል፤ ለዚችም ክፉ ትውልድ እንዲሁ ይሆንባታል።”

[46] ለሕዝቡም ይህን ሲነግራቸው፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።

[47] ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ መጥቶ ፥ “እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ከውጭ ቆመዋል፤ ሊያነጋግሩህም ይሻሉ ” አለው።

[48] እርሱ ግን ለነገረው መልሶ ፥ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው።

[49] እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ ፥ “እነሆ፥ እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው።

[50] በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴ፥ እናቴም ነውና ” አለ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters