[1] “ያንጊዜም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡ ዐሥሩን ደናግል ትመስላለች።
[2] ከእነርሱም ውስጥ አምስቱ ሰነፎች፥ አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
[3] ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ዘይት አልያዙም ነበር።
[4] ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮቻቸው ዘይት ይዘው ነበር።
[5] ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉም አንቀላፉና፥ ተኙ።
[6] መንፈቀ ሌሊት በሆነም ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራ መጣ፤ ልትቀበሉት ውጡ ’ የሚል ጩኸት ሆነ።
[7] ያንጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ነቁና መብራታቸውን አዘጋጁ።
[8] እነዚያ ሰነፎችም ልባሞችን ፥ መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
[9] ልባሞችም ፥ ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ የለም፤ ነገር ግን ወደሚሸጡ ሂዱና ለራሳችሁ ግዙ ብለው መለሱላቸው።
[10] ሊገዙም እንደ ሄዱ ሙሽራው መጣ፤ እነዚያም የተዘጋጁት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ ደጁም ተዘጋ።
[11] በኋላም እነዚያ ደናግል መጥተው ፥ አቤቱ አቤቱ ክፈትልን አሉ።
[12] እርሱ ግን መልሶ ፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አላውቃችሁም አላቸው።
[13] እንግዲህ ትጉ፤ የሰው ልጅ የሚመጣባትን ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና።
[14] “መንገድ እንደሚሄድ፥ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤
[15] ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ።
[16] ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ።
[17] እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ።
[18] አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታዉን ወርቅ ቀበረ።
[19] ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቈጣጠራቸው።
[20] አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ፥ አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ።
[21] ጌታውም ፥ መልካም፥ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
[22] ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ ፥ አቤቱ፥ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፍሁ አለ።
[23] ጌታውም ፥ መልካም፥ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንክ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
[24] አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ ፥ አቤቱ፥ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤
[25] ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ፥ መክሊትህ።
[26] ጌታውም መልሶ አለው ፥ አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ፥ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ፥ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን?
[27] ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር።
[28] ከዚያ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፤ ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት።
[29] ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል።
[30] ክፉውን አገልጋይ ግን፥ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት።
[31] “የሰው ልጅ በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል።
[32] አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው ይለያቸዋል።
[33] በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።
[34] ያንጊዜ ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ፥ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ።
[35] ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ሆኜ ተቀብላችሁኛልና።
[36] ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጐብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና።
[37] ያንጊዜም ጻድቃን መልሰው እንዲህ ይሉታል ፥ አቤቱ፥ መቼ ተርበህ አይተንህ አበላንህ? መቼስ ተጠምተህ አይተንህ አጠጣንህ?
[38] መቼስ እንግዳ ሆነህ አይተንህ ተቀበልንህ? መቼስ ታርዘህ አለበስንህ?
[39] መቼስ ታመህ አይተንህ ጐበኘንህ? መቼስ ታስረህ ወደ አንተ መጥተን ጠየቅንህ?
[40] ከዚህም በኋላ ንጉሡ መልሶ እንዲህ ይላቸዋል ፥ እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞች ለአንዱ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት።
[41] ከዚህም በኋላ በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ፥ እናንተ የተረገማችሁ ለሰይጣንና ለመልእክተኟቹ ወደተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ።
[42] ተርቤ አላበላችሁኝምና፤ ተጠምቼም አላጠጣችሁኝምና።
[43] እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፤ ታርዤም አላለበሳችሁኝምና፤ ታምሜም አልጐበኛችሁኝምና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ አልጠየቃችሁኝምና።
[44] ያንጊዜም በግራው ያሉት እንዲህ ብለው ይመልሳሉ ፥ አቤቱ መቼ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ፥ ወይስ እንግዳ ሆነህ፥ ወይስ ታርዘህ፥ ወይስ ታመህ፥ ወይስ ታስረህ አይተን አላገለገልንህ?
[45] ከዚህም በኋላ ንጉሡ እንዲህ ብሎ ይመልስላቸዋል ፥ “እውነት እላችኋለሁ ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ያላደረጋችሁትን ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም።
[46] እነዚያም ወደ ዘለዓለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ።”