Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 11:16

[1] እንዲህም ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር ከፈጸመ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው ፥

[2] “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።”

[3] ከዚህም በኋላ፥ የካህናቱ አለቆች ጻፎችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ስሙ ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ።

[4] ጌታችን ኢየሱስንም በተንኰል ይዘው ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ።

[5] “ነገር ግን፥ በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን ” አሉ።

[6] ጌታችን ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥

[7] ዋጋው እጅግ ብዙ የሆነ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብርሌ የያዘች ሴት ወደ እርሱ መጣች፤ ጌታችን ኢየሱስም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

[8] ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ ፥ “ይህች ሴት ለምን ይህን ያህል ሽቱ አጠፋች?

[9] ይህ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድሆች ምጿት ይሰጥ ዘንድ ይቻል ነበርና።”

[10] ጌታችን ኢየሱስም ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው ፥ “ይህችን ሴት ለምን ታደክሙአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና።

[11] ድሆችንስ ዘወትር ታገኙአቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ በጎ ታደርጉላቸዋላችሁ፤ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም።

[12] እርስዋ ይህን በራሴ ላይ ያፈሰሰችውን ሽቱ ለቀብሬ አደረገችው።

[13] እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት ቦታ ይህች ሴት ያደረገችው ለእርስዋ መታሰቢያ ሆኖ ይነገራል።”

[14] ከዚህም በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ የሚባለው የአስቆሮቱ ሰው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።

[15] “ምን ትሰጡኛላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ ” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት

[16] ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።

[17] ከፋሲካም በመጀመሪያው ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ቀርበው ፥ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ በየት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት።

[18] ጌታችን ኢየሱስም አላቸው ፥ “ወደ ከተማ ወደ እገሌ ዘንድ ሂዱ፤ መምህር ፥ ጊዜዬ ቀርቧልና ከደቀ መዛሙርቶቼ ጋር ፋሲካን በአንተ ዘንድ አደርጋለሁ ብሎሃል ” በሉት።

[19] ደቀ መዛሙርቱም ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካንም አዘጋጁ።

[20] በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።

[21] ሲበሉም ፥ “እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል ” አላቸው።

[22] እጅግም አዘኑ፤ እያንዳንዱም “አቤቱ፥ ምናልባት እኔ እሆን?” ይሉ ጀመር።

[23] እርሱም መልሶ እንዲህ አለ ፥ “ከእኔ ጋር እጁን ወደ ወጭቱ የሚያገባ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል።

[24] የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ በተሻለው ነበር።”

[25] አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ እንግዲያ እኔ እሆን?” አለ፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተ ራስህ አልህ ” አለው።

[26] ሲበሉም ጌታችን ኢየሱስ ኅብስቱን አንሥቶ፥ ባረከ፤ ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም “ይህ ሥጋዬ ነው እንኩ ብሉ ” ብሎ ሰጠ።

[27] ጿዉንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ ፥ “ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ።

[28] ኀጢኣትን ለማስተስረይ፤ ስለ ብዙዎች የሚፈስ፥ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።

[29] በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲሱን እስከምጠጣባት እስከዚያች ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።”

[30] መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

[31] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “በዚች ሌሊት ሁላችሁም ትከዱኛላችሁ፤ መጽሐፍ ፥ እረኛውን እገድለዋለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ ብሎአልና።

[32] ከተነሣሁም በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ።”

[33] ጴጥሮስም መልሶ ፥ “ሁሉም ቢክዱህ እንኳ እኔ ከቶ አልክድህም ” አለው።

[34] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” አለው።

[35] ጴጥሮስም ፥ “ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ አልክድህም ” አለው፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደ እርሱ አሉ።

[36] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ቦታ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ፥ “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ ድረስ በዚህ ተቀመጡ ” አላቸው።

[37] ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ወሰደ፤ ያዝንና ይተክዝም ጀመር።

[38] ከዚህም በኋላ ፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ተቀመጡ፤ ከእኔም ጋር ትጉ ” አላቸው።

[39] ከዚያም ጥቂት ፈቀቅ አለና በግንባሩ ሰግዶ ጸለየ፤ እንዲህም አለ ፥ “አባቴ ሆይ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጿ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም።”

[40] ወደ ደቀ መዛሙርቱም ሄደ፤ ተኝተውም አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው ፥ “አንድ ሰዓት እንኳ ከእኔ ጋር መትጋት እንዲህ ተሳናችሁን?

[41] ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ይሻልና፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

[42] ዳግመኛም ሄዶ፥ ጸለየ፤ እንዲህም አለ ፥ “አባቴ ሆይ ይህች ጿ ሳልጠጣት ከእኔ ልታልፍ የማይቻል ከሆነ ፈቃድህ ይሁን።”

[43] ዳግመኛም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፤ ተኝተውም አገኛቸው፤ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው ነበርና።

[44] ደግሞም ለሦስተኛ ጊዜ ትቶአቸው ሄደና ያንኑ ቃል ብቻ ደግሞ ጸለየ።

[45] ዳግመኛም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ እነሆ ጊዜው ደረሰ፤ የሰውንም ልጅ በኀጢኣተኟች እጅ አሳልፈው ይሰጡታል።

[46] ተነሡ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”

[47] ይህንም ሲናገር፥ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች ዘንድ ሾተልና ጎመድ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ።

[48] አሳልፎ የሚሰጠውም ፥ “የምስመው እርሱ ነው፤ እርሱን ያዙ ” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።

[49] ያንጊዜም ይሁዳ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ቀርቦ ፥ “መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ” አለና ሳመው።

[50] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ?” አለው፤ ያንጊዜም ቀረቡ፤ እጃቸውንም አንሥተው ጌታችን ኢየሱስን ያዙት።

[51] እነሆም፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና፤ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው።

[52] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ መልስ፤ ሰይፍን የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉና።

[53] ወይስ ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክትን አሁን ይልክልኝ ዘንድ አባቴን ልማልደው የማልችል ይመስልሃልን?

[54] እንዲህ ከሆነስ ፥ ይህ ሊሆን ይገባል የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዴት ይፈጸማል?”

[55] ጌታችን ኢየሱስም ያንጊዜ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው ፥ “እንደ ሌባ በሾተልና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? በመቅደስ ዘወትር ሳስተምር ከእናንተ ጋር እኖር ነበር፤ አልያዛችሁኝምም።

[56] ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው፤” ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።

[57] ጌታችን ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።

[58] ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ከሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥም ገብቶ የነገሩን መጨረሻ ያይ ዘንድ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ።

[59] የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች፥ ሸንጎውም ሁሉ ጌታችን ኢየሱስን ሊገድሉት የሐሰት ምስክሮች ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም።

[60] ብዙዎች የሐሰት ምስክሮችም መጡና አላገኙበትም፤ በኋላም ሁለቱ መጥተው ፥

[61] “ይህ ሰው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ላፈርሰው፥ በሦስተኛውም ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሏል ” አሉ።

[62] ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ ፥ “እነዚህ በሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው።

[63] ጌታችን ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ሊቀ ካህናቱም ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ትነግረኝ ዘንድ በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ ” አለው።

[64] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ከእንግዲህ ወዲህ የሰውን ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ ” አለው።

[65] ያንጊዜም ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀደደ፤ “እነሆ ተሳደበ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ትሹለታላችሁ? እነሆ፥ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” አለ።

[66] እነርሱም መልሰው ፥ “ሞት ይገባዋል ” አሉ።

[67] ከዚህም በኋላ በፊቱ ላይ ተፉበት፤ ራሱንም በዘንግ መቱት፤ ፊቱንም በጥፊ መቱት፤ እንዲህ እያሉ ፥

[68] “ክርስቶስ ሆይ ንገረን፤ በጥፊ የመታህ ማነው?”

[69] ጴጥሮስ ግን ከቤት ውጭ በግቢው ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ብላቴናም ወደ እርሱ መጥታ ፥ “አንተም እኮ ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ ” አለችው።

[70] እርሱም ፥ “የምትይዉን አላውቀዉም ” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ።

[71] ወደ በርም በወጣ ጊዜ ሌላዪቱ አየችውና ከዚያ ለቆሙት ፥ “ይህም እኮ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር ” አለቻቸው።

[72] ዳግመኛም ካደ፤ ያን ሰውም እንደማያውቀው ማለ።

[73] ከጥቂት ጊዜም በኋላ ቆመው የነበሩ መጡና ጴጥሮስን ፥ “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህም ያስታውቅብሃል ” አሉት።

[74] ያንጊዜም፤ ያን ሰው እንደማያውቀው ይምልና ይረገም ጀመር፤ ወዲያውኑም ዶሮ ጮኸ።

[75] ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” ያለውን የጌታችን የኢየሱስን ቃል አሰበ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters